የአትራኖስ ሚድያ ምስረታ አስፈላጊነት
ሚድያ ባለዉ ተቀባይነት፣ ተአማኒነት፣ ተደራሽነትና አዝናኝነት ባህሪዎች በዚህ በ21ኛዉ ክ/ዘመን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ያንዲትን አገር ማህበረ-ፓለቲካዊ ዕድል ላይ የሚኖረዉ አዎንታዊ ጫና በቀላሉ የሚታይ አደለም። ሚድያ ህዝብንና መንግስትን የሚያገናኝ ድልድይ፣ ገዢንና ሻጭን የሚያገናኝ ገበያ፣ አንድን ማሕበረሰብ ከሌላ ማሕበረሰብ ጋር የሚያስተሳስር መአድ በመሆኑ አስፈላጊነቱ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ከኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ማደግ ተያይዞ አለም ወደ ትንሽ መንደር በተቀየረችበትና መረጃ የጉልበትና የሃብት ምንጭ በሆነበት በዚህ ዘመን ወቅታዊ፣ ቀልጣፋና እዉነተኛ መረጃ በተለያየ መንገድና አቀራረብ ወደ ማህበረሰብ ለማድረስ ሚድያ ተተኪ የሌለዉ ወቅታዊ፣ ሃይለኛና አማራጭ የሌለዉ መሳርያ ነዉ። በዚህ መነፅር ሲታይ የትግራይ ሚድያዎች እድገት አንፃራዊ መሻሻል እንኳ ቢያሳይ በአገራችንና በዓለማችን ሚድያዎች እድገት መነፅር ሲታይ ግን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ያለ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። ስለዚህም ይህ መሬት ላይ እየተንፏቀቀ ያለዉን የሚድያ ሂደት ለመደገፍና ለትግራይንና ለትግራይን ህዝብ ዘብ የሚቆም ሚድያ ያለመኖር ላይ እየታየ ያለዉን ክፍተት ግምት ዉስጥ በማስገባት የሚድያ እጥረት በተቻለ መጠን ለመሙላት አትራኖስ ሚድያ ሟቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የአትራኖስ ሚድያ ስያሜ ምክንያትና ትርጉም እንዲሁም የአፈጣጠር እዉነታ
የአገራችንን ህልዉናና እድገት ሲፈተሽ ከክርስትናና ከእስልምና ሃይማኖቶች መግባትና መስፋፋት በእጅጉ የተቆራኘ ነዉ። ስለዚህም ስልጣኔ፣ ፍልስፍና፣ መንግስታዊ አስተዳደር፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ የባህል ህክምና መጀመርና ሌሎችም የሰዉ ልጅ ሂወት ዉስጥ መሳኝ የሆኑ መስተጋብሮች የክርስትና ሃይማኖት ጥንታዊ ድርሳናትና ብራና ዉስጥ አድገዉና ዘምነዉ እንዲሁም አገርና ታሪክ ገንብተዋል። የነዚህ ጥንታዊያን መፅሓፍት የእዉቀት ብርሃናቸዉ ወደ መላዉ ዓለም የሚዘረጋዉ ደግሞ አትራኖስ ተብሎ የሚጠራ ክቡር የመፅሓፍ መንበር ነዉ። ይህ አትራኖስ በዘመናዊዉ ዓለም ፓድየም (podium) በሚል ስያሜ ፓለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የኪነ-ጥበን ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ሌሎች በዓለም ዙሪያ በየሰዓቱ እዉቀትና መረጃ ለዓለም የሚያሰራጭበት የእዉቀት መድረክ ነዉ። ከዚህ ፅንሰ-ሓሳብ በመነሳት መረጃንና እዉቀትን በሚድያ መልክ ወደ ማህበረሰብ ለማድረስ የተነሳ ተቋም አትራኖስ በሚል ክቡር ስም መጥራት “ስም ይመርሆ ለግብሩ” እንደሚባለዉ ተግባሩንና አላማዉን መግለፅ ይችላል ከሚል አስተሳሰብ የተመረጠ ስም ነዉ።
የአትራኖስ ሚድያ ህጋዊነትና መስሪያ-ቤት
አትራኖስ ሚድያ በዋናነት ኢንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ በሚኖሩ ባለሞያዎችና የኮሚኒቲ አባሎች ተነሳሽነትና ድጋፍ የተመሰረት በመሆኑ ዋና መስሪያ-ቤቱ ለንደን ከተማ ሲሆን በእንግሊዝ አገር ሕግ መሰረት ህጋዊ ሰዉነት ኖሮት በUK መንግስት የሚታወቅና ካምፓኒ ሃዉስ ዉስጥ የተመዘገበ ነዉ። በቀጣይነት ደግሞ እንደየእድገቱ እየተገመገመ አዉሮፓ፣ ኢትዮጵያና ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የየአገሩ ሕጋዊ ሂደት እየተከተለ መስሪያ-ቤት የሚከፍት ይሆናል።
የአትራኖስ ሚድያ ዓላማ
አጠቃላይ የአትራኖስ ሚድያ ዓላማ ከላይ መግቢያዉ ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረዉ የትግራይ ህዝብ እድገት አሁን ባለንበት ሁነን ሲመዘን ይቅርና በትግሉና በመስዋእትነቱ ተጠቃሚ ሊሆን ይቅርና “ተገላቢጦሽ ዉሃ ወደላይ” እንደሚባለዉ እንደ ተራ ዜጋ እንኳ የፈለገዉ ቦታ ሄዶ ሊኖርና ሃብት ሊያፈራ የማይችልና ማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ከባድ አደጋ አንዣቦበት ይገኛል። አሁን ህዝባችን ገብቶበት ካለዉ የዘር ማጥፋት አድጋ ማዳን፣ በወራሪ ሃይሎች ምክንያት ተፈጥሮ ያለዉ ሰዉ ሰራሽ ረሃብ መታገልና አስፈላጊ የሚባለዉን መረጃ አዘጋጅተን ወንጀለኞቹን ወደ ፍርድ-ቤት ማቅረብ ዋናዉ የሚድያችን ዓላማ ሲሆን ጎን ለጎን ደግሞ በወራሪዎች የተዘረፈዉና የወደመዉ የትግራይ ህዝብ ሃብት ንብረት ወደ ቦታዉ መመለስና ያወደሟቸዉን ተቋማት በህግ ተይዘዉ እንዲተኳቸዉና እንዲመልሷቸዉ ማድረግ ነዉ።
ይህን ጊዝያዊ አደጋ መታገል የአትራኖስ ሚድያ አንድ ዓላማ ይሁን እንጂ የአትራኖስ ሚድያ ዋነኛዉና የረዥም ጊዜ ዓላማ ከዚህ የሰፋና ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ነዉ። በዚህ መሰረትም የአትራኖስ ሚድያ ዋና ዓላማ በማህበረሰባችን ማሃል የሚታዩ ጠቃሚ፣ አስተማሪና አኩሪ ፀጋዎችን መጠበቅ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ኋላ-ቀር አመለካከቶችና አስተሳሰቦችን በማከም ወደ ከፍተኛ የአመለካከቶችና የአስተሳሰቦች ምጥቀት በመሸጋገር አንድነቱን ጠብቆና አጠናክሮ የሚኖሩት ታሪካዊ ሃብቶች፣ ስነ-ማሕበራዊ ፀጋዎች (social capital)፣ ተፈጥሯዊ ሃብቶች (natural resources)፣ የተታሪ ሰዉ ሃይል ሃብት (human resource)ና ሌሎች ፀጋዎቹን በእዉቀት፣ በሳይንስና በጥበብ ተቀናጅቶና ተመርቶ ወደ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጥቅም በመቀየር ለልጆችዋ ብሎም ለጎብኚዎችዋ የምትመች ሰላማዊት፣ የሰለጠነች፣ የተከበረችና የታፈረች ትግራይ መፍጠር ነዉ።
የትግራይ አርሶ-አደር ከበሬ ወደ ትራክተር
እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወራሪ ሃይሎች ጦርነቱን ያወጁት የህዝባችን የጀርባ አጥንት የሆነዉ የትግራይ አርሶ-አደር ለማደህየት ሆን ብለዉ ዓመት ሙሉ የለፋበትን እህሉ በረሃ ላይ እያለ ነዉ። ያ በረሃ የነበረዉን እህል ወረዉ ወደ ኤርትራና ወደ አማራ ክልል ወስደዉታል። ሊወስዱት ያልቻሉትንም አቃጠለዉት ሄደዋል። ቀፎ ዉስጠ የቆየዉንም እህል እንዲያዉ። በተመሳሳይ ቤሮዎች ላሞችና ሌሎች የቤት እንስሳት አርደዉ በልተዉ፣ የትግራይ አርሶ-አደር ሞፈርና ቀምበር ሰብስበዉ እሳት አቃጥለዋል። በዚህም መሰረት የትግራይ አርሶ-አደር በዚህ ክረምት የተሟላ የእርሻ ስራ ለመስራትና እህል ለመዝራት እጅግ እየተቸገረ እንዳለ ግልፅ ነዉ። ይህን ከግምት ዉስጥ በማስገባት በሚቀጥለዉ ክረምት የትግራይ አርሶ-አደር ከባህላዊዉ በበሬ ጥንድ ማረስ ወጥቶ ወደ ዘመናዊ እርሻ ገብቶ በትራክተር ለማረስ የሚያስችለዉ ዓቅም ልንፈጥርለት ይገባል በማለት እላይ የተጠቀሰዉ ፕሮጀክት ጀምረናል። አሁን የማስተዋወቅ ሂደት ላይ ያለን ሲሆን አስተዋዉቀን ስንጨርስ ደግሞ በቀጥታ ገንዘብ ወደ ማዋጣት እንገባለን።