የአዲስ አበባ የ60ዎቹ የኪነ ህንፃ መለያዎች ‘እድሳት’ እና ያስነሳው ጥያቄ
በአዲስ አበባ አምባሳደር አካባቢ ከዋናው ፓስታ ቤት አጠገብ የሚገኘው ኪዳኔ በየነ ህንፃ ነጭና ሰማያዊ ቀለም መቀባት መጀመሩን ተከትሎ በከተሜውና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
የኪነ ህንፃውን ዲዛይን፣ የጣለው የታሪክ አሻራ፣ የበርካቶች ትውስታ (ትዝታ) አካል ስለሆነ የሚቀባው ቀለም ይዘቱን ስለሚቀይረውና ህንፃውን አዲስ መልክ ሊሰጠው አይገባም ብለው በርካቶች ተከራክረዋል።
በርካታ ህንፃዎች የራሳቸው አሻራ ያላቸው ሲሆን፤ አራት አስርት ዓመታት የኋሊት ሂደን ታሪክን በምንፈትሽበት ወቅት ኪዳኔ በየነ ህንፃ የዚያን ትውልድ ያስደነገጠ፣ ያሳዘነ እንዲሁም የኢህአፓን የትግል ታሪክ የቀየረ ክስተት ያስተናገደ ነው።
በበዙዎች ዘንድ የአብዮቱ ጠባቂ (ጋርዲያንስ ኦፍ ዘ ሪቮሉሽን) ተብለው የሚጠሩት ተማሪዎችም ሆነ የከተሜው ነዋሪ በ1969 የተፈጠረውን የሚዘነጉት አይመስልም። ኪዳኔ በየነ ህንፃ የኢህአፓው ታጋይ ተስፋዬ ደበሳይ ለመጨረሻ ጊዜ በህይወት የታየበት ስፍራ ነው።
ዓመቱ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለመግደል የተደረገው ሙከራ የከሸፈበት፣ ቀይ ሽብር የተፋፋመበት፣ ነጻ እርምጃ የተፈቀደበት፣ የቤት ለቤት አሰሳ የተጠናከረበት ወቅት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
መጋቢት 15/1969 ዓ.ም ተስፋዬ ደበሳይና በሪሁን ማርዬ ኪዳኔ በየነ ህንፃ ውስጥ ለመደበቅ በሚሞክሩበት ጊዜ በደርግ ጦር ተከበቡ።
በሪሁን ማርዬ ሲገደል ተስፋዬ ግን ህንፃው ስድስተኛ ፎቅ ላይ ደርሶ በመስኮት እራሱን ወረወረ። የኢህአፓው መሪም በዚህ መንገድ ህይወቱ ተቋጨ።
የአዲስ አበባ መለያ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ይህ ህንፃ ቀለም መቀባት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ የታሪክ ማኅደር መፈተሹ አልቀረም።
ቀለም እንዲቀባ የተወሰነው የኪዳኔ በየነ ህንጻ ብቻ ሳይሆን ነባሮቹ ሰንጋ ተራ የሚገኘው በድሉ ህንፃ፣ የፒያሳው ባንኮ ዲሮማ ይገኙበታል።
ነባሮቹ ህንፃዎቸ ቀለም ይቀቡ መባሉ በኪነ ህንፃ፣ በታሪክና በቅርስ ባለሙያዎች ዘንድ የህንፃዎቹን ይዘታት እንዲሁም ዲዛይን ማጥፋት ነው በሚል ተቃውሞ ቀርቦበታል።
በከተሞች ፈጣን ለውጥ ማኅበረሰቡ ያለፉ ትዝታዎችን እንዴት ይጠብቃል? የሚታወሰውን እና መረሳት ያለበትንስ ማንስ ይወስናል? የወደፊት ትዝታዎችስ እንዴት ይቆረቆራሉ? የሚለውም ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።
ህንፃዎቹን ቀለም መቀባትስ ይሄንን ያህል ለምን አከራካሪ ሆነ? ፋይዳቸውስ ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎችም በስፋት እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኪነ ህንፃ መምህርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ቀለም መቀባቱ ተገቢ አይደለም ይላሉ።
ምሁሩ የሚያነሱት የመጀመሪያው ነጥብ ቀለም ሊቀባበት የተሄደበት መንገድ ሙያዊ አካሄድ አለመከተሉን በማንሳት ነው።
“በቅርስነት የተመዘበ ወይም እንደነ ባንኮ ዲ ሮማ፣ ኪዳኔ በየነ፣ በድሉ ህንፃ እድሜ ጠገብ ህንፃዎች ቀለማቸው ይለወጥ ሲባል ሙያዊ አካሄድ አለው” የሚሉት አርክቴክት ዮሐንስ በቅርቡ ግን የተሞከረው ይህን እንዳልተከተለ ይናገራሉ።
ለአስርት ዓመታት ያህል እነዚህ ህንፃዎች የከተማው ዋነኛ መለያዎች ከመሆናቸው አንፃር በአካባቢው መልክነት የማይታወቅ አዲስ መልክ አዲስ ቀለም ማምጣት አንደኛ አካባቢውን እንደሚረብሸው ያስረዳሉ።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ህንፃዎቹ ታሪካዊ ዳራቸውን በመዳሰስም ይዘውት የኖሩትን ማንነት (አይደንቲቲ) ስለሚቀይረው በብዙ መልኩ የሚደገፍ አይደለም ይላሉ።
በዋነኝነት እነዚህ ህንፃዎች ማኅበረሰቡ የሚያውቃቸውና የተላመዳቸው ጠባይ አላቸው በማለትም ባለሙያው ያክላሉ።
“ያንን መልክ ጠብቆ ማቆየት ወይም እንዲጎላ ማድረግ እንጂ መቀየር፣ የኅብረተሰቡን የጋራ ትውስታ (ኮሌክቲቭ ሜሞሪ) ይለውጣል። እናም የባዳነት ወይም የእንግድነት ስሜት ይፈጥራል” ይላሉ።
ይህ እርምጃም በከተማ እቅድ ሙያ፣ በኪነ-ህንፃ፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ የሚመከር እንዳልሆነም ሙያዊ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ መኮንንም በአርክቴክት ዮሐንስ ሃሳብ ይስማማሉ፣ በዋነኝነት የሚያነሱት ሃሳብም ባለሙያዎችን ማማከር አንደሚገባ ነው።
በከተሞች ውስጥ ያሉ ህንፃዎች፣ ሐውልቶችም ሆነ ሰፈሮች የየራሳቸው የታሪክ አሻራ ከመኖራቸው አንፃር ባለሙያዎች የትኞቹ መታደስ፣ ቀለም መቀባት መፍረስ እንዳለባቸው ይወስናሉ ይላሉ።
ፕሮፌሰሩ እንዲህ አይነት የኪነ-ህንፃ፣ የታሪክ ተመራማሪዎች ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ካልተሳተፉ ጥፋት እንደሚከሰት የአጼ ምኒልክ ሐውልትን እንደገና ለማደስ የተደረገውን ሙከራ ይጠቅሳሉ።
ሐውልቱን እንደገና ለማደስ ሲሞከርም ቀለም ሊቀባ ሲልም ነሐስ አይቀባም ተብሎ ክርክር ቢቀርብም የሚሰማ አልተገኘም ይላሉ።
ነሐስ ተገቢው ሙቀት እየተሰጠው ተገቢው ኬሚካል ተመርጦ በነበረው መልኩ እንዲቆይ በሚያደርግ ቴክኒክ እንደታደስ ይናገራሉ።
ይህ ካልሆነ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም የሚሉት ፕሮፌሰሩ በተመሳሳይም በኪነ ህንፃ ውስጥም የራሳቸው መልክ ያላቸውና ህንፃዎች ተፈጥሯዊ ይዘታቸው ተጠብቆ ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ የተሰሩ የኪነ ህንፃ መልኮች አሉ እንዳሉ ይጠቅሳሉ።
ለምሳሌ ያህል የሂልተን ሆቴልን የሚያነሱ ሲሆን ቀድሞም ዲዛይናቸውና ሃሳባቸው እንዳይነኩ የተደረጉ ሲሆኑ መታደስም ካለባቸው በባለሙያዎች በመታገዝ መሆን ይገባዋል ይላሉ።
ምንም እንኳን ህንፃዎች የራሳቸው ታሪክና አሻራ ስላላቸው ሊጠበቁ ይገባል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ እነዚህ ህንፃዎች ቢፈርሱና አዲስ ቢሰራ እንዲሁም ቢታደሱም ሆነ ቀለም ቢቀቡ ለከተሞች የተለየ ውበት ይሰጣሉ የሚሉም አሉ።
ለአርክቴክት ዮሐንስ ችግሩ መታደሱ ሳይሆን እድሜ ያላቸው ህንፃዎች ነባር ይዘታቸውን ጠብቀው እንዴት ይታደሳሉ የሚለው ነው።
የህንፃዎቹ መታደስ እድሜያቸው እንዲረዝም፣ የሳሱ ቦታዎች ካሉ እንዲጠገኑ፣ የተበላሹ የግንባታ ቁሶች፣ በማርጀት ብዛትም የተሰባባሩ መስኮቶችና መጠገን ተገቢ ከመሆኑም በላይ አካባቢውን እንደሚያሳምረውም ጨምረው ያስረዳሉ።
ሆኖም ግን ሙያዊ ባልሆነ መልኩ ከታደሱ የህንፃውንም እድሜ እንደሚያሳጥረው በማስታወስም ያስጠነቅቃሉ።
ባንኮ ዲሮማ፣ በድሉ ህንፃ፣ ኪዳኔ በየነ ህንፃ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተሰሩና የ1960ዎቹ ተብለው የሚጠሩ ግንባታዎች ናቸው።
እነዚህ ህንፃዎች በዘመኑ የነበሩትን የኪነ ህንፃ ዲዛይን፣ የግንባታ ጥበብ፣ የግንባታ ቁሳቁስ አመራረጥ የሚያስተምሩና ዘመኑን የሚናገሩ መሆናቸውን አርክቴክት ዮሐንስ ያስረዳሉ።
“እነዚህ ህንፃዎች ቀለም ቢቀቡ አዲስ መልክ መስጠትና ዘመናቸውን መሻር ነው” ይላሉ።
“ጥንታዊ የሆነ የብራና መጽሐፍን ገነጣጥለን በወረቀት ብንለብደው ወረቀቱ የዚህ ዘመን ነው፤ ብራናው የጥንት ዘመን ነው” በማለትም ህንፃዎቹን ቀለም ሊቀባ የተሄደበትን የተሳሳተ አካሄድ በምሳሌ ያስረዳሉ።
እነዚህን ህንፃዎች ፓወር ጄት የሚባል የውሃ መርጫ፣ የስርገት መከላከያ መቀባትም ሆነ ይዘታቸውን እንደጠበቁ የሚታደሱበት መንገድ እንዳለ ያስረዳሉ።
“ቀለምም መቀባት ይቻላል ነገር ግን የሚቀባው ቀለም የጥንቱን ይዘትና መልክ ሳይቀይር ወይንም የእንግድነት ስሜት ሳያመጣ ሊሆን ይገባል” ይላሉ።
ፕሮፌሰር በቀለ በበኩላቸው ሁሉ ነገር መፍረስ አለበት ወይም ሁሉ ነገር ሊጠበቅ ይገባል በሚለው አይስማሙም። ባለሙያዎች መስፈርቶችን አውጥተው መነካት የሌለባቸውን ለይተው ለነገው ትውልድ እንዲነግሩ መቆየት አለባቸው ይላሉ።
አዳዲስ ነገሮች መሰራት እንዲሁም ዛሬ የተሰሩት የነገው ታሪክ አካል ከመሆናቸው አንፃር በመስፈሪያ ተለክተው ሊታዩ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
“ሁሉ ነገር አይፈርስም፤ ሁሉ ነገር አይቀርም። በዛሬው ብቻ ዘመን አልኖርንም። ትናንትናም ነበርን፤ አገራችንም እንደዛው፤ ወደፊትም ለመኖር ወደኋላ የነበረውን ማንነትን ለመግለጽ መኖር አለበት ትናንት። ለትናንት ደግሞ ህያው ምስክር ብቻ አይደለም፤ የተፃፈ አይደለም። ግዙፍ ነገር ያስፈልገናል” ይላሉ።
ህንፃዎች የራሳቸውን አሻራ እንደሚያስቀምጡ ማስታወስና የታሪክ አካልነታቸውን መረዳት አፅንኦት ሊሰጠው እንደሚገባም ይጠቅሳሉ።
ለሁለቱም ባለሙያዎች በዋነኝነት የሚጠቅሱት የሙያዊ ምክር አስፈላጊነትንና ከሙያው በተፃራሪ በሆነ መልኩ እንዳይሰራ ነው።
“ሁሉ ነገር ደርዝ አለው። የሚቀባው ለምንድን ነው? ቀድሞስ ቀለም ስለጠፋ ነው ወይ ሳይቀባ የቀረው?” በማለት የሚጠይቁት ፕሮፌሰሩ፤ ህንፃው ያልተቀባው በምክንያት እንደሆነና የተሰራበት ሁኔታ የማያብለጨልጭ፣ የማይደበዝዝ፣ በቋሚነት ተፈጥሯዊ መልኩን ይዞ እንዲቀመጥ ታስቦም ነው ይላሉ።
የህንፃው አሰራር ሂደት፣ ህንፃው የተሰራበት ቁሶች፣ ታሪካዊ ዳራም ሆነ ዲዛይነሩን ከግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ በማስታወስም “ማማር ደርዝ አለው” ይላሉ።
በአንድ ወቅት የበድሉ ህንፃን ያሰሩት ይልማ በድሉ ልጅ በድሉ ይልማ ከአገር ውስጥ ሚዲያ ጋር በተደረገ ቆይታ አባታቸው ህንፃውን ሙሉ ቀን እዚያው ሲያሰሩ ይውሉ እንደነበርና አርክቴክቱም ጣልያናዊ እንደሆነ አውስቷል።
በድሉ ህንፃ በወቅቱ በነበረው ዘመናዊነትም በአፄ ኃይለ ሥላሴ የቀኝ አዝማችነት ማዕረግም እንደተሰጣቸው አቶ በድሉ ተናግረዋል።
በድሉ ህንጻን የሰራው ጣልያናዊ አርክቴክት በአዲስ አበባም ሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጣልያን አርክቴክት አይደለም።
ጣልያኖች አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ ከሶስት ወራት በኋላ ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ ከፍተኛ እቅድ ነበራቸው።
በተወሰነ መልኩም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ነጮችና የከተሜው ነዋሪ የማይቀላቀሉበት ሰፈሮችንም ለመፍጠር ተሞክሯል።
ምናልባትም በአምስት ዓመቱ ወቅት ለ ኮርቡዚየር የተባለው ጣልያናዊ አርክቴክት የአዲስ አበባ የከተማ ማስተር ፕላን እውን ቢሆን ኖሮ በሃያኛው ክፍለ ዘመን በከፍተኛ ጭካኔ ከታቀዱ ከተሞችና አንዷም በሆነች ነበር።
ለ ኮርቡዚየር ለጣልያን ቅኝ ግዛት ኢምፓየር አዲስ ከተሞች ምን አይነት ዲዛይን ያስፈልጋል በሚልም ለሙሶሎኒ በፃፈው መልዕክት ላይ ኢትዮጵያ እንደ ታቡላ ራሳ (ባዶ ሰሌዳ) አድርጎ ነበር የሳላት።
ጣልያን አቅዳው የነበረው ተግባራዊ የዞን ክፍፍልም ሆነ ስር ነቀል ለውጦች ተግባራዊ ባይሆኑም በርካታ ጥለዋቸው ያለፉት የኪነ-ጥብብ አሻራዎች አሉ።
የበድሉ ህንፃም ሆነ የኪዳኔ በየነ ህንፃ፣ ባንኮ ዲሮማና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህንፃ በአውሮፓ ሞደርኒስት አርክቴክቸር (ዘመናዊ ኪነ-ህንፃ) የሚለውን የሚወክሉና በወቅቱም እንደነበረው አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን የያዘ ዘይቤ እንደሆነ አርክቴክት ዮሐንስ ይናገራሉ።
በዓለም ላይ ሞደርኒስት ኪነ-ህንፃ ዘይቤ ሲያብቡ የተገነቡና ቦልድ የሆነ ቅርፅ እንዳላቸውም ያስረዳሉ።
ህንፃዎቹ ቀለማቸው ኧርዝ ወይም ከአካባቢያቸው ጋር የተስማሙ፤ አካባቢያቸውን የሚመስሉ በተጨማሪ ሻካራ የሆኑ (ቴክስቸር) ያላቸው ናቸው ይላሉ።
የተሰሩበት ቁስም ቀድሞ ፋብሪካ ውስጥ ለብቻ ተዘጋጅተው፣ ወይንም ተጋግረው (ፕሪፋብሪኬት) የተለጠፉ ክላዲንግ ቁሶች ናቸው።
ከዚህ በላይ የግንባታ ጥበባቸው እጅግ ጥንቃቄ የሚታይበት ወይንም ልቅም ብለው የተሰሩ ከመሆናቸው አንፃር በልስንና ቀለም ይቀቡ ቢባል ያንን ከፍተኛ ጥንቃቄ ወይንም ልቅም ብሎ መሰራት ሊጠበቅ አንደማይችል አበክረው ይናገራሉ።
“ያንን ትውስታውን፣ ቀለሙን፣ ይዘቱ ሲታጣ ህንፃው ተቀይሯል፤ ሌላ ህንፃ ነው። የድሮው ህንፃ አይደለም፤ ስለዚህ ህንፃው ቢቀየርም ችግር የለም ካልን ግን ከቅርስ ሳይንስ ውጪ ነው የምንሆነው” ይላሉ ዮሐንስ።
በተለያዩ አገራት አንድን ህንፃን ሳይሆን አካባቢውና ከተማው ጭምር የሚጠበቅበት አካሄድ አለ ለዚህም የሕንዷን ኒው ደልሂና ኦልድ ደልሂ መጥቀስ ይቻላል።
በአውሮፓ አንዳንድ ከተሞችም በነባር ህንፃው አካባቢ አዲስ ህንፃ የሚገነባ ከሆነ እንግዳ እንዳይሆን ወይም ነባሩን እንዳይቃረን የሚቀባው ቀለም አይነት፣ የህንፃው መልክና ሌሎች ጉዳዮች ይዘት እንደሚወሰን አርክቴክት ዮሐንስ ያብራራሉ።
በአዲስ አበባ ያሉ ህንፃዎችና ቅርሶች ለበርካታ ዓመታት መከራከሪያ ሆነው ቆይተዋል። አዲስ አበባን ከመለወጥ ጋር ተያይዞ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን መገንባት፣ ለነዋሪው የጋራ ግንባታ፣ መንዶችና መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ በርካታ የጠፉ ቅርሶች እንዳሉም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ነገር ግን ዮሐንስ እንደሚሉት በመንግሥት በኩል ያለውን አቅጣጫ ሲመለከቱት አዲስ መልክ ሰጥቶ የማስደመም ፍላጎት እንጂ ” ይህ ሁኔታ በተደራጀና ሆን ብሎ ቅርስን የማጥፋት ነው ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ ምክንያቱም በቅርብ ተሳትፌ አይቻለሁ” ይላሉ።
ሆኖም የሚሰራበት መንገድ ችኮላና ጥድፊያ የበዛበት እንዲሁም ባለሙያን የማማከሩ ልምድ ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ይገልጻሉ።
“የማስደመም ዝንባሌው ይህንን ጥፋት አስከትሏል። እንጂ ሆን ተብሎ ታሪክን የመቀየር፣ የአዲስ አበባን መልክ ለማበላሸት ነው ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ” ይላሉ።
ከሰሞኑ ከህንፃዎቹ ቀለም መቀባት ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ ውጤት ያፈራ ሲሆን የኪዳኔ በየነ ህንፃ የቀለም ቅብ ባለበት እንዲገታ ተደርጓል። የተቀባው የህንፃ ክፍል ወደነበረበትም ለመመለስ ምክከር እየተደረገም መሆኑም ተጠቅሷል።