በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ቀናት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከ70 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተመዘገበ።
ከጤና ሚንስቴር እና ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ማክሰኞ መስከረም 4/2014 ዓ.ም. ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የ34 ሰው ሕይወት አልፏል።
ሰኞ መስከረም 3/2014 ዓ.ም. ደግሞ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የ38 ሰዎች ሕይወት አልፎ፤ በሁለቱ ቀናት ውስጥ ብቻ 72 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
በወረርሽኙ ምክንያት ሕይወታቸው ከሚያልፍ ሰዎች በተጨማሪ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲሁ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ ነው።
ከሰሞኑ በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ እና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የጨመረው ‘ዴልታ’ በተባለው አዲስ አይነት የቫይረሱ ዝርያ ስርጭት ምክንያት መሆኑን የጤና ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ሦስተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደተከሰተ መልክት በታየባት ኢትዮጵያ፤ “ዴልታ” የተሰኘው አዲስ የኮቪድ ዝርያ መገኘቱንም የጤና ሚንስቴር ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር።
የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደሚለው ይህ ‘ዴልታ’ የኮቪድ ዝርያ ከሌላው የቫይረሱ ዝረያ ሁለት እጥፍ የመስፋፋት አቅም ያለው ሲሆን የሚያስከትለው ህመምም ከፍ ያለ ነው።
‘ዴልታ’ የተባለው ይህ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሁሉንም የዕድሜ ክልል የሚያጠቃ፣ ለከባድ ህመምና ሞት የሚዳርግ በተለይም ባልተከተቡ ሰዎች ላይ የሚበረታ መሆኑ ተነግሯል።
- የሠሜን ወሎና የዋግ ኸምራ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ
- በዓለም ዙሪያ በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ‘መኒ ሄይስት’
- የቻይናው አምባሳደር ከዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ ታገዱ
- በታሊባን መሪዎች መካከል ውጥረት መንገሱ ተሰማ
የጤና ሚንስቴር ዲኤታው እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ‘ዴልታ’ በተሰኘው የቫይረሱ ዝርያ የሚያዙ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
ሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን አለመከበር የቫይረሱ ስርጭት እንዲስፋፋ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከ30 በላይ የሞት መጠን የተመዘገበው ባለፈው ዓመት 2013 ሚያዝያ ወር የመጨረሻ ሳምንታት ላይ ነበር።
ሚያዝያ 19 ላይ 35 ሰዎች፣ ሚያዝያ 20 ላይ 34 ሰዎች እንዲሁም ሚያዝያ 25 እና 30/2013 ዓ.ም. ላይ ከበሽታው ጋር በተያያዘ 31 ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚንቴር አስታውቆ ነበር።
አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ‘ዴልታ’
ከቀናት በፊት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ ቀደሞ ካለው የከፋ መሆኑን ተናግረዋል።
‘ዴልታ’ የተሰኘው የኮሮናቫይረስ ዝርያ የኮቪድ-19 ክትባት በወሰዱ ሰዎች ላይ የሚኖረው ጉዳት ዝቅተኛ ስለሆነ ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባቶችን እንዲወስዱ ይመከራሉ።
መንግሥት የኮሮናቫይረስ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት በመቀጠሉ የጤና ሚኒስቴር ከጥቂት ሳምንት በፊት በሽታውን ለመከላከል መወስድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ያወጣውን መመሪያ በማሻሻል በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆን አዟል።
ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባት የሚሰጣቸው ዜጎች የዕድሜ ገደብ ዝቅ ከመደረጉ በተጨማሪ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲካተቱ ተደርጓል።
የኮሮናቫይረስ ክትባት በኢትዮጵያ መሰጠት ሲጀምር ክትባቱ በቀዳሚነት ለጤና ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ሆኖ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው እንዲሰጥ ቅድሚያ ተሰጥቶ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋባት በመዲናዋ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደር እድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስተሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀው ነበር።
በኢትዮጵያ የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረ አንስቶ አስከ ትናንት መስከረም 4 2014 ዓ.ም. ድረስ 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ክትባት ወስዷል።
የአሜሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል በኮቪድ ስርጭት ምክንያት ኢትዮጵያን “ደረጃ ሦስት” በሚል የጉዞ ማስጠንቀቂያ ከሰጠባቸው አገራት ውስጥ ትናንት አካቷል።
የአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹ “ደረጃ ሦስት” ውስጥ ወደ ተመደቡ አገራት አስገዳጅ ያልሆነ ጉዞ እንዳያደርጉ ይመክራል።
የኮቪድ-19 የበለጠ የከፋባቸው አገራት ደግሞ “ደረጃ አራት” ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፤ የአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹ ወደነዚህ አገራት እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የክትባት ፍትሐዊነት
የዓለም ጤና ድርጅት አፍሪካ ከቀሪው ዓለም ጋር ስትነጻጸር በኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት አቅርቦት “ወደኋላ ቀርታለች” ሲል አስጠነቀቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመው ግብ መሠረት ባለንበት የፈረንጆች ዓመት 40 በመቶ የሚሆነውን ሕዝባቸውን መከተብ የሚችሉት የአፍሪካ አገራት ሁለት ብቻ ናቸው።
ይህም ከሌሎች የዓለም አህጉራት ሁሉ በጣሙን ዝቅተኛው ነው ብለዋል፤ ዶ/ር ቴድሮስ።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት እስካሁን በዓለም ዙሪያ ከ5.7 ቢሊየን በላይ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች የተሰጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለአፍሪካ የደረሰው ግን 2 በመቶው ብቻ ነው።
ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረውም ክትባቶቹ በፍትሐዊ ሁኔታ ካልተከፋፈለ ቫይረሱ ባህሪዩን እንዲቀይር የሚያደርግ ከፍተኛ ዕድል እንዳለ አስጠንቅቀዋል።