በአፍጋኒስታን አዲስ መንግሥት ለመመሠረት የሚደረገውን ጥረት ተከትሎ በታሊባን መሪዎች መካከል አለመግባባት መንገሱን አንድ ከፍተኛ የታሊባን ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
አለመግባባቱ ከታሊባን መስራቾች መካከል አንዱ በሆኑት ሙላ አብዱል ጋኒ ባራዳር እና በካቢኔ አባላቱ መካከል ቤተ-መንግሥት ውስጥ መከሰቱንም ምንጮች ተናግረዋል።
ከሰሞኑ የባራዳርን ከሕዝብ እይታ መጥፋት ተከትሎ በታሊባን አመራሮች መካከል አለመግባባቶች መከሰታቸውን የሚያመላክቱ ያልተረጋጋጡ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።
ባሳለፍነው ወር አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረው ታሊባን አገሪቱን «እስላማዊ ኢምሬት» ሲል ማወጁ ይታወሳል። አዲሱ ጊዜያዊ ካቢኔም ሙሉ በሙሉ ወንድ ሲሆን በታሊባን አንጋፋ ሰዎች የተዋቀረ ነው።
አንድ የታሊባን ምንጭ ለቢቢሲ ፓሽቶ እንደገለፀው ባራዳር ካሊል ኡር ራህማን ሃቃኒ ከተሰኙት የስደተኞች ሚኒስትር እና በታጣቂው የሃቃኒ ኔትዎርክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ካላቸው ግለሰብ እና ተከታዮቻቸው ጋር የተጋጩ ሲሆን ጠንካራ ቃላትንም ተለዋውጠዋል።
- የሠሜን ወሎና የዋግ ኸምራ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ
- በርካቶች በአንድ ላይ የወደዱት ‘መኒ ሄይስት’
- የሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ከፕሬዝዳንቱ ግድያ ጋር በተያያዘ ከሀገር እንዳይወጡ ታገዱ
- በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ላይ ስለኢትዮጵያ ምን ተባለ?
መቀመጫውን በኳታር ያደረገ አንድ የታሊባን ከፍተኛ አባል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ያለው ምንጭም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ክርክሩ መከሰቱን አረጋግጧል።
አዲሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባራዳር በጊዜያዊ መንግሥታቸው አወቃቀር ደስተኛ ባለመሆናቸው ክርክሩ ተነስቷል ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል። ክፍፍሉ በተለይም በአፍጋኒስታን ለተገኘው ድል ማን እውቅናውን ይውሰድ በሚል የተነሳ መሆኑንም ምንጮቹ ተናግረዋል።
ሚስተር ባራዳር ትልቁ ትኩረት እንደ እሱ ባሉ ሰዎች በተመራው የዲፕሎማሲ ስራ ላይ መሆን አለበት ብሎ የሚያምን ሲሆን፤ የሃቃኒ ቡድን አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ግን ድሉ በውጊያ የተገኘ ነው የሚል አቋም ይዘዋል ተብሏል።
ባራዳር በ2020 ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የስልክ ውይይት በማድረግ በቀጥታ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር የተነጋገረ የመጀመሪያው የታሊባን መሪ ነበር። ከዚያ በፊት የአሜሪካ ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ እንዲወጣ በዶሃ የተደረገውን ስምምነት ፈራሚም ነበር።
በሌላ በኩል የሃቃኒ ቡድን በቅርብ አመታት በአፍጋኒስታን ኃይሎች እና በምዕራባውያን አጋሮቻቸው ላይ ከተሰነዘሩ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳል። ቡድኑ በአሜሪካ የሽብርተኛ ድርጅት ተብሎም ተፈርጇል።
የታሊባን ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት ባራዳር ከካቡል ወጥተው ወደ ካንዳሃር ከተማ ሄደዋል። ባራዳር ባሳለፍነው ሰኞ በተለቀቀው የድምፅ ቅጅ «በጉዞ ላይ እንደነበረ» ተናግሯል። «በአሁኑ ሰዓት የትም ብሆን ሁላችንም ደህና ነን» የሚል መልክትም ሰፍሮበታል። ቢቢሲ ይህንን የድምጽ ቅጂ ለማረጋገጥ አልቻለም።
ታሊባን ምንም አይነት ግጭት አልተፈጠረም ሲል አስተባብሏል። እንዲሁም ባራዳር ደህና መሆናቸውን ቢገልጽም እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ መግለጫዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ባራዳር የታሊባንን ጠቅላይ መሪን ለማግኘት ወደ ካንዳሃር ሄደዋል ብለው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ለቢቢሲ ፓሽቶ «ስለደከማቸው እረፍት ለማድረግ ፈልገው ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ታሊባን እ.ኤ.አ በ 2015 የቡድኑ መስራች መሪ የነበሩትን ሙላህ ኡመርን ሞት ከሁለት ዓመት በላይ መሸፈኑ ይታወሳል። በእነዚህ ዓመታትም በስሙ መግለጫዎችን መስጠታቸውን ቀጥለው ነበር።
ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለፁት ባራዳር ወደ ካቡል ይመለሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ማንኛውም ክርክር እንዳልተከሰተ ለመካድ በካሜራ ሊታዩ ይችላሉ። በአደባባይ ታይተው የማይታወቁት የታሊባኑ ጠቅላይ መሪ ሂባቱላህ አኽንድዛዳን የተመለከቱ በርካታ መላ ምቶች እየተሰጡ ይገኛሉ።
ግለሰቡ የታሊባን የፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች መሪ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአፍጋኒስታን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትላንት ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ አለም አቀፍ ለጋሾች ወደ አፍጋኒስታን የሚያስገቡትን ዕርዳታ በድጋሚ እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል።