ባለፉት ሁለት ወራት ሱዳን ውስጥ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ከ80 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ይህ በአገሪቱ ውስጥ በጎርፍ ምክንያት በሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው የክረምቱ ወር ከጀመረበት ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ሲሆን በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አድርሷል።
የሱዳን ብሔራዊ የአደጋ መከላከያ ምክር ቤት ቃል አቀባይ በተከታታይ ወራት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያሰከተለውን ጉዳት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ በአጠቃላይ 84 ሰዎች መሞታቸውንና 67 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።
ከሐምሌ ጀምሮ በአገሪቱ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ አገሪቱ ካሏት 18 ግዛቶች መካከል ቢያንስ በ14ቱ ውስጥ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
- “የአማራ ብቻ ሳይሆን የጋምቤላ፣ የሲዳማና ደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች ቤንሻንጉል ጉሙዝ ገብተዋል”
- በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ላይ ስለኢትዮጵያ ምን ተባለ?
- ጦርነት ያፈናቀላቸው የሠሜን ወሎ እናቶችና ህጻናት ፈተና
የጎርፍ አደጋው በሰዎች ላይ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር ከ30 ሺህ በላይ ቤቶች ላይ ውድመትን ሲያደርስ፤ በማሳ ላይ የነበሩ ሰብሎች እንዲሁም መሰረተ ልማቶችም ላይ ከባድ ጉዳት አስከትሏል።
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ ካባድ ዝናብና ጎርፍ ሱዳን ውስጥ ስላደረሰው ጉዳት ባወጣው መረጃ ላይ እንዳመለከተው፤ 102,000 የሚሆኑ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት የውሃ እጥረት ሊጋጥማት እንደሚችል ስጋቷን ስትገልጽ የቆየችው ሱዳን በግዛቷ ውስጥ በሚጥለው ከባድ ዝናብና በአባይ ወንዝ አማካይነት በሚመጣው ጎርፍ ምክንያት ችግር እያጋጠማት ነው።
ባለፈው ዓመት አገሪቱ ባጋጠማት ከባድ የጎርፍ አደጋ 100 ሰዎች ሲሞቱ ከ100,000 በላይ ቤቶች ወድመውባት ከ600,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ለችግር ተጋልጠው ነበር።
በዚህም ሳቢያ ለሦስት ወራት የቆየ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋ በአደጋው የተጎዱ ዜጓቿን ለመርዳት ጥረት ስታደርግ እንደነበር ይታወሳል።