11 መስከረም 2021

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከጽህፈት ቤታቸው ዋይት ሐውስ በወጣ መግለጫ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን ገለጹ።
ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በራሳቸውና በባለቤታቸው ጂል ባይደን ስም ባስተላለፉት መልካም ምኞታቸው ላይ በአዲሱ ዓመት ሰላም እንዲወርድ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ያስተላለፉት ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ አገራት የዘር ሐረጋቸው ለሚመዘዝ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ አሜሪካውያን ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ መልዕክታቸው ላይ ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች የወጡ ሪፖርቶች በእጅጉ እንዳሳሳባቸው ገልጸው፤ አስተዳደራቸው በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከአጋሮቻቸው ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ሰላምን ማምጣት ቀላል እንዳልሆነ ነገር ግን በውይይት ሊጀመር እንደሚችል በመግለጽ “ታላቋና ባለብዝሃ ሀብቷ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የገጠማትን መከፋፈል እንደምትወጣውና በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም በማድረግ እየተካሄደ ያለውን ግጭት እንደምትፈታው እናምናለን” ብለዋል።
- በ2013 የኢትዮጵያ ፖለቲካ አበይት ኹነቶች የትኞቹ ነበሩ?
- የተሰናባቹ 2013 ዓመት ዓበይት ምጣኔ ሀብታዊ ክስተቶች
- 2013 በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ወሳኝ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት
- ግድቡ በቀጣይ ወራት በሁለት ተርባይኖች እስከ 750 ሜጋዋት ኃይል ያመነጫል ተባለ
በመልዕክታቸውም ላይ በአማርኛ “መልካም አዲስ ዓመት” በማለት በዓሉን ለሚያከብሩ በሙሉ የተመኙት ፕሬዝዳንት ባይደን “አዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በዓለም ዙሪያ ላሉ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች ሰላም፣ እርቅ እና ፈውስ የሚመጣበት እንዲሆን እጸልያለሁ” ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ በዋናነት ያተኮረው በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ አስር ወራትን ያስቆጠረውና ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ላይ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ ሰላም እንዲወርድና ችግሩ በድርድር እንዲፈታ ጥሪ ሲያቀርብ እንዲሁም መልዕክተኞችን ወደ አካባቢው ሲልክ ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ባይደንን ጨምሮ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በስልክና በአካል ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን አሜሪካ ግጭቱን በተመለከተ የምታወጣቸው መግለጫዎችና የምትወስዳቸው እርምጃዎች ወገንተኝነት ያለበትና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ነው በሚል ሲተች ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነትና በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ጉዳዮችን በቅርበት እንዲከታተሉላቸው ጉምቱውን ዲፕሎማት ጄፍሪ ፌልትማንን ሾመው ወደ አካባቢው በተደጋጋሚ ጉብኝት አድርገው ከባለሥልጣናት ጋር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።