7 መስከረም 2021

ከ20 ዓመት በፊት። በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር መስከረም 1። የእንቁጣጣሽ ቀን።
ዓለም ከወደ አሜሪካ በመጣ አንድ ከባድ ዜና ተናጠች። በርካቶች አፋቸውን በእጃቸው ሸፍነው የቴሌቪዥን መስኮታቸው ላይ አፈጠጡ።
አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን እየተንደረደረ ልክ እንደ ሆሊዉድ ፊልም ግዙፍ ሕንፃ ላይ ተሰካ። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ሌላ አውሮፕላን እየገሰገሰ መጥቶ በሌላኛው ሕንፃ ላይ ተላተመ።
አሜሪካ መስከረም 1/1994 ዓ. ም (እአአ መስከረም 11/2001) የደረሰባትን እንዲሁ ልትረሳው የምትችለው አይደለም። እነሆ የዚህ አስከፊ የሽብር ጥቃት 20ኛ ዓመት በመዘከር ላይ ይገኛል።
አውሮፕላኖቹን ጠልፎ ከግዙፎቹ ሕንፃዎች ጋር እንዲላተሙ ያስገደደው ሰው ጥቃቱን ከመፈፀሙ በፊት ሊቆም ይችል ነበርን?
ፍራንክ ፔሌግሪኖ ማሌዢያ ካለ አንድ የሆቴል ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ይህንን አሰቃቂ አደጋ ቴሌቪዥኑ ላይ ይመለከታል። ዜናውን ባለማመን ሲመለከት የነበረው ፍራንክ “በፈጣሪ ስም! ይህማ ካሊድ ሼኽ ሞሐመድ መሆን አለበት” ሲል ለራሱ ተናገረ።
ፍራንክ ይህን ሊል የቻለበት ምክንያት አለው።
የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ድርጅት (ኤፍቢአይ) የቀድሞው መርማሪ ሞሐመድን ለሦስት አስርታት ሲፈልገው ቆይቷል። ነገር ግን ከመስከረም 11ዱ ጥቃት ጀርባ እንዳለ የሚታመነው ሞሐመድ አሁንም ፍርድ አላገኘም።
- የመስከረም አንዱ ጥቃት ሲታወስ፡ አልቃኢዳ የት ነው ያለው?
- አልቃኢዳ በአሜሪካ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ዕለትና ከዚያ በኋላ የሆነው ምን ነበር?
- በአፍጋኒስታን በአየር ጥቃት የሚሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ነው ተባለ

የሞሐመድ ጠበቃ ፍርድ እስኪሰጥ ድረስ ሌላ 20 ዓመት ሊፈጅ ይችላል ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
እርግጥ ነው ይህ ጥቃት በደረሰ ወቅት የአል-ቃዒዳ መሪ የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ከመስከረም 9/11 ጥቃት ጋር ስሙ በስፋት ይያያዛል።
ነገር ግን ጥቃቱን በጥልቀት የመረመሩ ሰዎች የጥቃቱ አድራጊ ፈጣሪ ሞሐመድ አሊያም ኬአስኤም እየተባለ የሚጠራው ሰው ነው ይላሉ። ዕቅዱን አርቅቆ ወደ አል-ቃዒዳ የወሰደው ሞሐመድ እንደሆነ ይታመናል።
የተወለደው ኩዌት ነው። በ1980ዎቹ አፍጋኒስታን ገብቶ ውጊያ ከመጀመሩ በፊት አሜሪካ ውስጥ ተምሯል።
የመስከረም 11 ጥቃት ከመድረሱ በፊት የኤፍቢአይ መርማሪው ፍራንክ ፔሌግሪኖ አክራሪውን ሞሐመድ እንዲከታተል ኃላፊነት ይሰጠዋል።
የሞሐመድ ስም በኤፍቢአይ መዝገብ ላይ የሰፈረው በፈረንጆቹ 1993 ዎርልድ ትሬድ ሴንተር የተባለው ሥፍራ ላይ ከደረሰው የቦንብ ጥቃት በኋላ ነው። ኤፍቢአይ፤ ሞሐመድ በጥቃቱ ከተሳተፉ ለአንዱ ገንዘብ አስተላልፏል ሲል ካለበት ተለቅሞ እንዲመጣ ያዛል።
በ1990ዎቹ አጋማሽ ፍራንክ፤ ሞሐመድን ኳታር አግኝቶት በቁጥጥር ሥር ሊያውል ከጫፍ ደርሶ ነበር። ስለሱ ብዙ ያጠና የነበረው ፍራንክ ሰውዬው ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችን ለመምታት ዕቀድ እንዳለው ደርሶበታል።
ፍራንክና ሌሎች የኤፍቢአይ መኮንኖች ሞሐመድን በካቴና ቀፍድደው እንዲያመጡ ይታዘዛሉ። ይህንን ተከትሎ ወደ ኦማን ይበራሉ። ወደ ኳታር ገብተው ሞሐመድን ያሳድዳሉ።
ፍራንክ ኳታር ወደሚገኘው የአገሩ ኤምባሲ ይሄድና ሞሐመድን አስሮ ለመውሰድ የእስር ፈቃድ ይዞ እንደመጣ ይነግራቸዋል። የኤምባሲው ሰዎች ግን ሰውዬውን ለመያዝ ግርግር መፍጠሩ አስፈላጊ አይደለም የሚል እምነት ነበራቸው።
ከቆይታ በኋላ አምባሳደሩ የኳታር ባለሥልጣናት ሞሐመድ እንዳመለጣቸው ነግረውኛል ሲሉ ለፍራንክ ይነግሩታል። “ሞሐመድን ለመያዝ ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ እንደማይገኝ ስለምናውቅ በጣም ተበሳጭተን ነበር” ይላል ፍራንክ።
የፎቶው ባለመብት,GETTY IMAGESየምስሉ መግለጫ,
እአአ 1993 በዓለም የንግድ ማዕከል ላይ የተፈጸመው ቦምብ ጥቃት ስድስት ሰዎችን ገድሎ ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑትን አቁስሏል።
አሜሪካዊያን እንደሚፈልጉት መረጃ ሳይደርሰው ያልቀረው ሞሐመድ ኳታርን ጥሎ አፍጋኒስታን ይገባል።
ከዚህ በኋላ ባሉ ዓመታት የሞሐመድ ስም በየቦታው መነሳት ይጀምራል። በሽብር ጥቃት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ስልክ ውስጥ የሞሐመድ ስም አይጠፋም።
ይሄኔ ነው ሞሐመድ ዕቅዱን ነድፎ ወደ ኦሳማ ቢን ላደን ያቀናው። ዕቅዱ አውሮፕላን ጠልፎ ኒው ዮርክ ከሚገኙት ግዙፍ መንትያ ሕንፃዎች ጋር ማላተም ይላል።
ዕቅዱም ተሳክቶ የመስከረም 11ዱ ጥቃት እውን ሆነ። የፍራንክ ጥርጣሬ እውን የሆነው አንድ በቁጥጥር ሥር ያለ የአል-ቃዒዳ አባል የጥቃቱ አድራጊ ፈጣሪ ሞሐመድ ነው ባለ ጊዜ ነው።
“ሞሐመድ ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለ ባወቅን ወቅት እንደኔ ቅስሙ የተሰበረ የለም” ይላል ፍራንክ።
ከጥቃቱ ሁለት ዓመታት በኋላ በፈረንጆቹ 2003 ሞሐመድ ፓኪስታን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ፍራንክ በስተመጨረሻ ሞሐመድ ለፍርድ ቆሞ ሊያየው ቋምጧል። ነገር ግን ሞሐመድ ደብዛው ጠፋ።
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሞሐመድን “ብላክ ሳይት” እየተባለ ወደሚጠራ አድራሻው ወደማይታወቅ የምርመራ ጣቢያ ወሰደው።
“የሚያውቀውን ማወቅ እፈልጋለሁ። በፍጥነት መረጃ ማግኘት እሻለሁ” ብለው ነበር በወቅቱ የሲአይኤ ነባር ባለሥልጣን የሆኑ ሰው።
ሰውየው በርካታ ጥቃቶችን እንዳቀነባበረ መናዘዙ ተነገረ። ነገር ግን የአሜሪካ ሴኔት በኋላ እንዳረጋገጠው ተጠርጣሪው ፈፅሜያቸዋለሁ ብሎ ያመናቸው ወንጀሎች አብዛኛዎቹ የፈጠራ ናቸው።
ሲአይኤ ምርመራውን አጠናቆ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ሞሐመድ ወደ ጓንታናሞ ቤይ ጥብቅ እሥር ቤት ተዘዋወረ። ኤፍቢአይም ሰውየውን እንዲያገኘው ፈቃድ ተሰጠው።
ወርሃ ጥር 2007 ፍራንክ ፔሌግሪኖ ለዓመታት ሲያሳድደው የነበረው ሞሐመድን ፊት ለፊት ተገኝቶ አየው።
ሞሐመድ ወዲህኛው ጫፍ ፍራንክ ደግሞ በወዲያኛው ሆኖ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ተፋጠጡ።
“በ90ዎቹ የእስር ማዘዣ ይዤ እያሳደድኩት እንደነበር እንዲያውቅ ፈለግኩኝ” ይላል ፍራንክ። የቀድሞው የኤፍቢአይ መኮንን ከዚህ የዘለለ ስለነበረው ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ባያካፍልም “አመናችሁኝም አላመናችሁኝ፤ ሰውዬው በጣም ንግግር አዋቂና ቀልደኛ ነበር” ይላል።
ፍራንክ እንደሚለው ሞሐመድ ባደረገው ነገር ምንም ዓይነት ፀፀት የሚሰማው ሰው አይደለም። ይልቁንስ ችሎት ፊት በመቅረብ የሰው ትኩረት መሳብ የሚወድ ሰው ነው።
የሞሐመድ ፍርድ ጥቃቱ በደረሰበት ኒው ዮርክ ለሕዝብ ክፍት በሆነ መድረክ እንዲሆን ሐሳብ ቀርቦ ነበር። ነገር ግን ሕዝቡና ፖለቲከኞች ሰውየውን ማየት ስለማይሹ እዚያ ጓንታናሞ እንዲሆን ተደረገ።
የሞሐመድ ፍርድ እየተጓተተ ቆይቶ ጓንታኖሞ ውስጥ ባለ አንድ ወታደራዊ ችሎት ውስጥ እንዲከናወን ሆነ። ነገር ግን በውጣ ውረዶችና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ታጅቦ አሁንም ሰውየው ፍርዱን አላገኘም።
የሞሐመድ ፍርድ ሂደት በዚህ ሳምንትም እንደሚቀጥል ቢጠበቅም መጨረሻው ግን ገና ይመስላል።
የሞሐመድ ጠበቃዎች በዚህ ሳምንት የሚከናወኑት ችሎቶች ለመስከረም 11ዱ ጥቃት 20ኛ ዓመት ዝክር የሆነ ነገር እየተከናወነ እንዳለ ለማሳየት ነው ይላሉ።
የሞሐመድ የፍርድ ሂደት አሁንም ማስረጃ ማቅረብና ምስክር መስማት ላይ እንጂ ወደ መጨረሻው ፍርድ ገና አላመራም።
የተጠርጣሪውን ፍርድ እንዲከታተሉ አንድ አዲስ ዳኛ ቢሾሙም ዳኛው ከሳቸው በፊት ሲሰሙ የነበሩ 35 ሺህ ገፅ ያላቸው ሰነዶችን ማገላበጥ ይጠበቅባቸዋል።
የፍርድ ሂደቱን አከራካሪ ያደረገው አንደኛው ምክንያት ሞሐመድና ሌሎች አራት ተጠርጣሪዎች ሲአይኤ በድብቅ በሚያስተዳድራቸውና “የላቀ የምርመራ ሂደት” ይጠቀምባቸዋል በተባሉ ካምፖች ውስጥ መቆየታቸው ነው።
በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ያለፉ ተጠርጣሪዎች ብዙውን ጊዜ ችሎት ፊት ሲቀርቡ ጥፋታቸውን ያመኑት በደረሰባቸው ስቃይ ምክንያት እንደሆነ ለችሎቱ ስለሚናገሩ የፍርድ ሂደቱ ይጓተታል።
ሌላኛው የሞሐመድን ፍርድ ያጓተተው ጉዳይ የአሜሪካ መንግሥት ሰዎች በሞት እንዲቀጡ መፈለጉ እንደሆነ ይታመናል።
ፍራንክ ከኤፍቢአይ ጡረታ ለመውጣት ካሰበበት ጊዜ ሦስት ዓመት አራዝሞ ጡረታ የወጣው የሞሐመድን ፍርድ መጨረሻ ለማየት በመሻት ነበር።
ነገር ግን የጡረታ ዕድሜው በመድረሱ ለዓመታት የሠራበትን መሥሪያ ቤት ጥሎ ለመውጣት ተገዷል።
ለዓመታት ሲያፈላልገው የነበረው ግለሰብ አሁንም ፍርድ ሳያገኝም አልፎም በአሜሪካ ታሪክ ላይ ከባድ ጠባሳ አሳርፎ ሲያይ ምናልባት በቁጥጥር ሥር አውየው ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ አይከሰትም ይሆን ነበር ሲል ይንገበገባል።
“ስሙ ሁልጊዜ ጭንቅላቴ ውስጥ ያቃጭላል። ይረብሸኛል” ይላል ፍራንክ።
“እንግዲህ ጊዜ ሁሉን ይፈታው ይሆናል።”