የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲቀጥልና ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነትም ላይ በአስቸኳይ እንዲደርሱ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ሁኔታውን እንዳሳዘናት ገልጻለች።
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ በውሃ መብት እና ልማት ላይ መግለጫ ማውጣቱ እንዳሳዘናት እንዲሁም ምክር ቤቱ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን ማየት እንደሌለበት አስፍራለች።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ለግልጽ ውይይት ከቀረበ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት የሦስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት እንዲካሄድ መወሰኑ ኢትዮጵያ በበጎ መልኩ የምትቀበለው ነው ብሏል።
ሆኖም የፀጥታው ምክር ቤት በሕዳሴ ግድብ ላይ ግልጽ ውይይት ካደረገ ከዘጠኝ ሳምንታት በኋላ መግለጫ ማውጣቱ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ እንደሆነም ተገልጿል።
የፀጥታው ምክር ቤት በፕሬዚዳንቱ በኩል በትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ሦስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ሙሌትና አሰራር ላይ በተመጣጣኝ የጊዜ ገደብ ውስጥ ስምምነት እንዲደረስ ድርድሩ እንዲቀጥል አገራቱን አበረታቷል።
በተለይም የቱኒዚያ የምክር ቤቱን መግለጫ ወደፊት መግፋቷ “ታሪካዊ የተሳሳተ እርምጃ” እንዲሁም በምክር ቤቱ አፍሪካን በጊዜያዊነት ወክላ አባል የመሆን ኃላፊነትንም ያዳክማል ብላለች ኢትዮጵያ።
ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ በተመለከተ የቱኒዚያን ምክረ ሐሳብ እንዳይቀበል መጠየቋ የሚታወስ ነው።
የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ተወስዶ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት ዋና አሸማጋይነት እንዲፈታ ውሳኔ መሰጠቱንና የምክር ቤቱ አባል ሆነችው ቱኒዚያ በድጋሚ ልታስገባ ያሰበችው ውሳኔ ሐሳብ የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እንደሆነ ኢትዮጵያ ገልጻ ነበር።
- የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የጎላ ሚና አይኖረኝም አለ
- የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ
- ግብጽ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመርን ተቃወመች
ሆኖም መግለጫውን በማቀናበር የምክር ቤቱ የአሠራር ዘዴ ታማኝነትን የሚፃረሩ ጥሰቶችን ለማስተካከል አስተዋጽኦ ያበረከቱትን የምክር ቤት አባላትም ኢትዮጵያ አመስግናለች።
በተጨማሪም የድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች የጋራ ጥቅምን እና ክልላዊ ትብብርን እውን ለማድረግ ዕድል እንደሚሰጥ አመልክታለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት አቋም ትክክለኛ እና ሕጋዊ መብቷን እውን ለማድረግ እንዲሁም በተፋሰሱ አገራት ሕዝቦች መካከል መተሳሰብን ለመገንባት ያለመ እንደሆነም አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ የአባይ ተፋሰስ አገሮች የሚተባበሩበትና የሚደጋገፉበት ጊዜ አሁን ነው ብላ የምታምን መሆኗን አስታውቃ በፕሬዚዳንታዊ መግለጫው መሠረት ሊነሱ የሚችሉ ማናቸውንም ጥያቄዎች ኢትዮጵያ እውቅና አትሰጥም ብሏል መግለጫው።
የፀጥታው ምክር ቤት በውሃ መነሻዎች እና በወንዞች ላይ በቴክኒካዊ እና አስተዳደራዊ አለመግባባቶች ውስጥ ብቃት የሚመለከተው አካል እንዳልሆነ በመግለጫው ጠቅሶ አገራቱ በ2015 የተፈረመውን የመርሆዎች ስምምነትን መሰረት በማድረግ ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ ጠይቋል።

“የፀጥታው ምክር ቤት ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን የድርድር ሂደት ገንቢ እና ተባባሪ በሆነ መንገድ እንዲያራምዱ ጥሪ አቅርቧል” ብሏል መግለጫው።
ከዚህ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የደኅንነት አካል በሦስቱ ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ታዛቢዎች በሕዳሴ ግድብ ላይ “የታዩ ቴክኒካዊ እና ሕጋዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ድርድሩን መደገፍ እንዲቀጥሉ” ጋብዟል።
ምንም እንኳን ለዓለም ሰላም ዋነኛ ሚና ባለው የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የድንበር ተሻጋሪ ወንዝና ግድብ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መቅረቡ የተለያዩ አስተያየቶች ቢያስነሳም፤ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት መወያያ ነበር።
ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያለ የፀጥታው ምክር ቤት ማንኛውንም ተሳትፎ ትተቻለች፣ አለመግባባቱን የአፍሪካ ሕብረት በተሻለ ሁኔታ መፍታት ይችላል ትላች።
ግብፅ በበኩሏ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ ዓለም አቀፍ ሰላምን እና ደኅንነትን ለመጠበቅ ያሳየውን ቁርጠኝነት እንዲሁም አባል አገራቱ በግድቡ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ልዩ ትኩረት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ላይ የሚኖረውን ከባድ እንድምታ ዕወቅና የሰጠ ነው ስትል አሞካሸታዋለች።
መግለጫው ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ሙሌትና እና አሰራር ላይ አስገዳጅ የሕግ ስምምነት ላይ እንድትደርስ የሚገፋፋ መሆኑንም አረጋግጧል ብላ ግብፅ እንደምታምን የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ጄነሬተር አንቀሳቃሽ አካል (Rotor) የመግጠም ሥራ ረቡዕ መስከረም 05/2014 በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ ተገልጿል።
በቅርቡ ኃይል እንደሚያመነጩ ከሚጠበቁት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለት ክፍሎች መካከል በዩኒት 10 ላይ የተርባይን ጀነሬተር ተሽከርካሪ አካል (Rotor) በቦታው ላይ የማስቀመጥ ሥራ መከናወኑንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።
ሮታሩና አብረው ያሉት አካላት 840 ቶን ክብደት ያላቸው ሲሆን ሮተሩ ብቻውን 780 ቶን እንደሚመዝን፣ ሮተሩ ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ ያለው አጋማሽ ርዝመት ወይም ዳያሜትር 11 ነጥብ 7 ሜትር መሆኑ ተገልጿል።
የሮተሩና የተርባይን አካላቶች በአግባቡ መገጠም የኃይል ማመንጨት የሙከራ ሥራ ለመጀመር መቃረቡ አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ግንባታው ከተጀመረ 10 ዓመት የሞላው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራው ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን በቅርቡ የመጀመሪያ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተገልጿል።
በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ግድቡን በተመለከተ ለዓመታት ሲደረግ የቆየው ድርድር መቋጫ ሳያገኝ አስከ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት መድረሱ ይታወሳል።
በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ለወራት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን መልሶ እንዲጀመር በወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሼኬዲ አማካይነት ጥረት እየተደረገ ነው።