11 መስከረም 2021

ዮናስ ግርማ በሥጋ ንግድ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ቆይቷል። ሥራውን ከወላጅ አባቱ ተረክቦ እያስተዳደረ ይገኛል። ዮናስ የሚያስተዳድረው ሥጋ ቤት በአዲስ አበባ ዝናን ካተረፉ አንጋፋ ሥጋ ቤቶች መካከል ነው።
ሥጋ ቤቱ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ በኢትዮጵያ ባላንጣ የሚባሉ ፖለቲከኞች ከሩቅ እየተያዩም ቢሆን የሚያዘወትሩት መሆኑ ነው።
ይህ በተለይም በቀድሞው የኢሕአዴግ ሥርዓት አሳዳጅ እና ተሳዳጅ የነበሩ ፖለቲከኞች የእግዜር ሰላምታ ተለዋውጠው እና ተቀላልደው ይመገቡበታል።
የጨርጨር ሥጋ ቤትን አሁን ላይ የሚያስተዳድረው ዮናስ ግርማ እንደሚለው “እነ አባይ ፀሐሃዬ፣ እነ ጌታቸው ረዳ በአንድ በኩል፤ እነ አንዷለም አራጌ በሌላ በኩል” ፊት ለፊት እየተያዩ ሥጋ ይቆርጡ ነበር።
“አንድ ጊዜ እነ ፕሮፌሰር መስፍን እና እነ ጌታቸው ሰላም ሲባባሉ ‘ምናለ ሥጋ ላይ እንደምትቻቻሉ ፖለቲካው ላይ እንዲህ ብትቻቻሉ’ ሰዎች ሲሉ ትዝ ይለኛል” ሲል ዮናስ ያስታውሳል።
አሁንም ቢሆን የተቃዋሚውም ይሁን የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ፓርቲ ሰዎች “ይተያያሉ፤ ሰላም ይባባሉ፤ ይበላሉ” ሲል ዮናስ ያስረዳል።
በእርግጥ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ባህሎች ቢፈተሹ መዐድ ለብቻ መቁረስን ከራስ ወዳድነት ወይም ከስግብግብነት ጋር ማቆራኘታቸውን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም።
እንዲያውም በአንድ ገበታ ላይ መቋደሱ እንደ ዋነኛ የቤተሰብ ብሎም የወዳጅነት ትስስር መንገድ ተደርጎ ይታያል።
የከተሜነት መስፋፋትን ተከትሎ ይህ በአንድ ገበታ ከቦ የመመገብ ልምድ እየቀነሰ ቢመጣም ቁርጥ ሥጋን ለብቻ መመገብ እምብዛም የማይስተዋል ነገር ነው።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እየጨመረ የመጣው የቁርጥ ሥጋ ፍቅርም፣ በአንድ ገበታ ከቦ የመመገብ ልምድን አጠናክሮ መቀጠሉን በሥራው ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይናገራሉ።
- መመጣጠን ያልቻለው የንግድ ሚዛን ጉድለትና የናረው የውጭ ምንዛሪ
- የሼፎች የበዓል ምግብ ምርጫ፡ ሼፍ ዮሐንስ፣ ጆርዳና እና ዮናስ
- የዓሳ ጥሬ ሥጋ እንደ በሬ ቁርጥ የሚቸበቸብባት ሐዋሳ
- ምግብ ወሲብን የተሻለ ያደርጋል?

ምርጥ የቁርጥ ሥጋ የት አካባቢ ይገኛል?
“የበሬውም ሆነ የገበሬው የኋላ ታሪክ ይጠናል” ሲል ዮናስ ጥሩ ሥጋ ለማግኘት ሥጋ ቤቶች ስለሚሄዱበት ርቀት ያብራራል።
“በዓለም ላይ ምርጡ ሥጋ አለ የሚባለው ጃፓን ነው። አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ሥጋ ከጃፓን ሥጋ አይተናነስም። ጥራትን አንጻር ፉክክር መጨመሩም ዋጋውን ሰቅሎታል” ይላል።
የከብቱን የኋላ ታሪክ ማጥናት የሚያስፈልገው እንደ ኮሶ ያሉ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል ነው ይላል ዮናስ።
“አንድ ከብት ታስሮ ከደለበ እና ወደ ውጪ ካልወጣ ኮሶ አያገኘውም። የኮሶ በሽታ በግምት እስከ 80 በመቶ ቀንሷል።”
“ከዚህ ቀደም ሥጋ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። አባቶቻችን ከብት ሲገዙ ምን በላ የሚለውን አይጠይቁም ነበር። አሁን የሚበላው ምግብ ለጤና ያለውን ተስማሚነት ጭምር አጥንተን ነው የምንገዛው። እንዲያውም እሱም አላረካ ብሎን ራሳችን ከብቱን ወደ ማደለብ ደረጃ ደርሰናል” ሲል ዮናስ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በዝርያ ምርጫ ግን የሐረርን ሰንጋ የሚያክል የለም ሲል ዮናስ ይናገራል። ቀጥሎ ጅሩ ይመጣል። የሐረር ሰንጋ ሥጋውን ጣፋጭ የሚያደርገው የአየር ንብረቱ ብሎም የሚደልብበት ስልት እንደሆነ ያብራራል።
“የሐረር ገበሬ ከብትን ከቦታ ቦታ እያዟዟረ ሳይሆን ቤት ውስጥ በእህል ነው የሚያደልበው። በአብዛኛው እማወራዋም አባወራውም የየራሳቸው አንድ አንድ ከብት ይኖራቸዋል። ለልጆቻቸው የሚሰጡትን እህል ነው ለከብቶቹ የሚመግቡት” ይላል ዮናስ።
“በርግጥ ጅሩም አንደዚሁ ነው። ግን ትንሽ አካባቢ ስለሆነች ሰፊ አቅርቦት የለም። ክብደት እንደውም የጅሩ ይበልጣል። ጥራት የሐረር ሰንጋ ቢበልጥም። ሐረር ሰፊ ስለሆነ እና ከብቶቹ ቶሎ ቶሎ ስለማይሸጡ ትንሽ የመቆየት እድል አላቸው” ሲል ያነጻጽራል።
ማባያው
ዮናስ ወደ ቁርጥ ሥጋ ሥራ ሲገባ ማባያው ባዶ ሚጥሚጣ እንደነበረ ያስታውሳል። አሁን ግን አዋዜው እንኳን በቄንጥ እንደሚዘጋጅ ነው የሚናገረው።
“አሁንማ አዋዜ ራሱ በጠጅ፣ በደረቅ ጠጅ እና በበሰለ ጠጅ ተብሎ ነው የሚቀመመው። በዚያ ላይ ከተለያየ የአገራችን ክፍል ቆጭቆጫ እና ዳጣ ይመጣል። አሁን አሁን ደግሞ ጥሬ ሥጋ በቆጮ ተጀምሯል” የሚለው ዮናስ ይህ የሥራው እድገት መገለጫ ነው ይላል።

የቁርጥ ሥጋ ዋጋ ለምን እንዲህ ናረ?
ዮናስ ከ20 ዓመታት በፊት ወደ ሥራው ሲቀላቀል የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ “ከ12 ብር ወደ 13 ብር” እየተጓዘ ነበር። “ያኔ ተወደደ የሚል ከባድ ተቃውሞ ነበር። በጣም ከባድ ተቃውሞ። አባቴ ሥራውን ሲጀምር አንድ ኪሎ ሥጋ አምስት ብር ነበር” ሲል ዮናስ ያስታውሳል።
ወላጅ አባቱ በደርግ ጊዜ የሳንቲም ጭማሪ አድርገዋል በሚል ታስረውም ነበር።
በተጠናቀቀው ዓመት 2013 ሚያዝያ 24 ተከብሮ ከዋለው ፋሲካ በዓል በፊት ጥሩ የቁርጥ ሥጋ በአዲስ አበባ 500 ብር አካባቢ ይሸጥ ነበር። አሁን ይህ እጥፍ ሆኗል። ከ900 እስከ 1000 ብር ድረስ ኪሱ ውስጥ የሌለው ሰው ቁርጥ ሥጋ መብላት አይቻለውም።
የጨርጨር ሥጋ ቤቱ ዮናስ እንደሚለው ከሆነ በሬው የሚበላው መኖ መወደዱ፣ ብሎም በሬዎቹ የሚደልቡበት መንገድ መቀየሩ የቁርጥ ሥጋ ዋጋ ሰማይ እንዲነካ አድርጎታል።
አንድ ከብት ከገበሬው ከተገዛ በኋላ ከአምስት እስከ ሰባት ወር ድረስ በሥጋ ቤቱ እንደሚደልብ እና በቀን የሠራተኛ ወጪን ጨምሮ አንድ በሬ እስከ ሁለት መቶ ብር ድረስ እንደሚፈልግ ዮናስ ይናገራል። በወር ስድስት ሺህ ብር ማለት ነው።
- ለሰው ልጅ ምርጡ ምግብ እንቁላል ይሆን?
- ከኑሮ ውድነት ጋር ግብ ግብ የገጠሙት የመንግሥት ሠራተኞች
- ኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን ለመግታት የባንኮች የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን በእጥፍ እንዲያድግ ወሰነች
“አንድ ኪሎ በቆሎ በፊት ሰባት ስምንት ብር ነበር የሚሸጠው። አሁን ከ30 ብር በላይ ይሸጣል። የተልባ ፋጉሎ አንድ ኪሎ 700 ብር ነበር። አሁን 3ሺህ 500 ብር ገብቷል” ይላል ዮናስ።
የንግድ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው አንደኛ ደረጃ የሐረር ሰንጋ በአዲስ አበባ 75 ሺህ ብር ሲሸጥ ሁለተኛ ደረጃው 50 ሺህ ብር ያወጣል።
የአርሲ ባሌ ከብት ሻሸመኔ ላይ 3ሺህ 500 ብር ሲሸጥ፣ የአፋር ፍየል ዴራ ላይ 3ሺህ 800 ብር ይሸጣል። ድብልቅ ዝርያ ያለው ፍየል አዳማ ላይ 5 ሺህ ብር ያወጣል ሲል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያሳያል።
ጥሬ ሥጋ እና የአልኮል መጠጥ
ጥሬ ሥጋ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትልልቅ ሰዎች የሚመገቡት ምግብ ተደርጎ እንደሚታሰብ ዮናስ ይናገራል። አሁን ላይ ግን ሴቶች እንዲሁም ወጣቶች የሚያዘወትሩት ምግብ ሆኗል።
ከሥጋ ጋር ከሚዘወተሩት መደበኛ መጠጦች በተጨማሪ “ተከሽኖ” የተሰኘ እና ጥሬ ሥጋን ተንተርሶ የሚጠጣ የአልኮል መጠጥ እስከመፍጠር ተደርሷል።
የቢራ፣ የወይን የአልኮል መጠጥ ብሎም የፍራፍሬ ውህድ የሆነው ይህ መጠጥ ከሥጋ ቤት አስተናጋጆች አልፎ አሁን አዋሽ የወይን ጠጅ ራሱን የቻለ ምርት እስከማስተዋዋቅ ደርሷል።

ቁርጥ ሥጋ በጤና ላይ ያለው ተጽኖ ምንድነው?
ቁርጥ ሥጋ መመገብ ከሚያስከትላቸው ዋነኛ የጤና ችግሮች መካከል አንዱ የኮሶ በሽታ ነው። በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ችግሩ የየዕለት መሆኑን ተከትሎ ባህላዊ የኮሶ መድኃኒት መጠቀም የተለመደ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የኮሶ በሽታ የጠፋ እስኪመስል ድረስ መቀነሱን በርካቶች ይናገራሉ።
የኮሶ ትል፣ ሳልሞኔላ እና አንትራክስ የተሰኙት በሽታዎች ከጥሬ ሥጋ ጋር ተያይዞ ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል። የእንስሳት ህክምና ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ደመቀ ወንድምአገኝ እንደሚሉት በሬውን ከማደለብ ጀምሮ ለምግብ እስከሚቀርብ ድረስ ባለው ጊዜ ያለው ንጽህና ካልተጠበቀ ለእነዚህ ህመሞች ሊያጋልጥ እንደሚችል ይናገራሉ።
እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥጋ ቤቶች ከብቶችን በራሳቸው በረት ማደለብ በመጀመራቸው እና ተዋህሲያንን የሚገድሉ መድሃኒቶች ለከብቶቹ ስለሚሰጡ ሥጋውም ጤናማ እንደሚሆን ባለሞያው ያስረዳሉ።
እንዲሁም በልምድ የቁርጥ በሬ ሲገዛ የሚመረጥበት መንገድ ከእንስሳ ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች ማኅበረሰቡን ጠብቋል ብለው ዶክተር ደመቀ ያምናሉ።
እንደ አንትራክስ ያሉ ገዳይ የሚባሉት በሽታዎችን ለመከላከል መንግሥት ዓመታዊ ክትባቶችን ጨምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉ ለበሽታዎቹ መቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ሐኪሙ ያክላሉ።
ጨምረውም አገራዊ በሽታን የመቆጣጠር አቅም ብሎም የገበሬዎች እውቀቱ መጨመር ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ጥሬ የበሬ ሥጋን መመገብ በኢትዮጵያ የተለመደ ይሁን እንጂ፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም ጥሬ የአሳ ሥጋ መመገብ የተለመደ ነው።
ጥሬ ሥጋን መመገብ ጥሬ አሳን ከመመገብ ጋር ሲነጻጸርም የጤና ስጋቶቹ ያነሱ መሆናቸውንም ዶ/ር ደመቀ ይናገራሉ። እንደውም በተዋሕሲያን የተበከለ ጥሬ አሳን በመመገብ የሚከሰቱ ህመሞች ገዳይ መሆናቸውንም ያክላሉ።
“ቀይ ሥጋ ውስጥ ያለው ፕሮቲን በተለይ በኩላሊት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። ስለዚህ ቀይ ሥጋ ተቀቅሎም ቢሆን ጥሬውን መመገብ ለጤና የሚመከር አይደለም” የሚሉት ዶ/ር ደመቀ ቀይ ሥጋን መመገብ በአየር ንብረት ላይም ጫናን እንደሚያሳድር ያስረዳሉ።
“ቀይ ሥጋን ማምረት በጣም ውድ ነው። አንድ በሬ ለማደለብ እስከ አራት ዓመት ቢፈጅም የሚገኘው ሥጋ ግን 200 ኪሎ ገደማ ነው። አንድ ኪሎ ቀይ ሥጋ ለማምረት እስከ 35 ሺህ ሊትር ውሃ ድረስ እንደሚያስፈልግ ጥናቶች ያመላክታሉ” ሲሉ የእንስሳት ሕክምና ባለሞያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዘወተረ ስለመጣው የፍየል ቁርጥ እና ከእሱ ጋር ተያይዞ ስለሚነሱ መላምቶችን በተመለከተ ባለሞያውን ጠይቀናቸዋል።
“ፍየል በቆላማ ቦታ ስለሚረባ ሌሎች እንስሳት የማይመገቡትን ቅጠላ ቅጠል ይመገባል። ታዲያ ከእነዚህ ቅጠሎች መካከል መድኃኒትነት ያላቸውን ቅጠሎች ስለሚመገብ ሥጋውም ፈዋሽ ነው የሚል መላ ምቶች አሉ። ነገር ግን ይህንን የሚያረጋግጥ ጥናት ግን እስካሁን አልተመለከትኩም።”
ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን በአግባቡ መከላከል እስከተቻለ ድረስ ጥሬ ሥጋን ተከትሎ የሚከሰት የተዋሕሲያን ችግርን ባግባቡ መቀነስ እንደሚቻል ባለሞያው አክለዋል።
በእርግጥ ዶ/ር ደመቀም የጥሬ ሥጋ ወዳጅ ናቸው።
“አምስት ስድስት ዓመት ጥሬ ሥጋ በተከታታይ ተመግቤአለሁ። ከተዋሕሲያን ጋር የተያያዘ ምንም አይነት ህመም ገጥሞኝ አያውቅም” ሲሉ የግላቸውን ልምድም ይናገራሉ።
ነገር ግን ቀይ ሥጋን መመገብን በተመለከተ እየተካሄዱ ያሉ ጥናቶች እንደሚያመለከቱት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያዘነብላል። ለዚህም ይመስላል በተለይም በበለጸጉት አገራት ሰዎች ወደ ነጭ ሥጋ ማዘንበል የመረጡት። የዶሮ እና የአሳ ሥጋ ማለት ነው።
ሕገ ወጥ እርድን መቀነስ ከተቻለ እና በሬው ሲደልብ እና ለምግብ ሲቀርብ ባለው ጊዜ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ ከተቻለ የተዋሕሲያን ስጋቶችን መቀነስ ይቻላል ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።