መስከረም 11/2001 ዓለምን የለዋወጠ ክስተት የተፈጠረበት ቀን ነው። የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ እና ወታደራዊ የኃይል ሚዛን የተፈተነበት ዕለት።
አሜሪካ ውስጥ አራት የተጠለፉ አውሮፕላኖች ከሕንፃ ጋር ተላትመው 2,996 ሰዎች ሞተዋል።
የ9/11ዱ የሽብር ጥቃት አሜሪካ በታሪኳ ከገጠሟት የሽብር ጥቃቶች ሁሉ የከፋው ነው።
ጥቃቱ የደረሰው ከ20 ዓመታት በፊት ቢሆንም አሉታዊ ተጽዕኖው እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። አሜሪካ ከዚህ ጥቃት በኋላ “ሽብር ላይ ጦርነት አውጃለሁ” ብላ አፍጋኒስታን እና ኢራቅን ወራለች።
የዛሬ 20 ዓመት ጥቃቱ ሲደርስ የነበሩትን 149 ደቂቃዎች እንዲህ ቃኝተናል።
- የመስከረም 11 ሽብር ጥቃት ‘አድራጊ ፈጣሪ’ እንዴት ከኤፍቢአይ አፍንጫ አመለጠ?
- የቦይንግ ዳይሬክተሮች ከ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ጋር በተያያዘ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው
- ታሊባን በማሕበራዊ ሚድያው ‘ጦርነት’ እንዴት ሊሳካለት ቻለ?
07:59
የአሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላን የሆነው ኤኤ11 ከቦስተን ሎጋን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሎስ አንጀለስ በረራ ጀመረ።
ከአውሮፕላን አብራሪው እና ከረዳቱ በተጨማሪ 9 የመስተንግዶ ሠራተኞች ነበሩ።
ከ81ዱ ተሳፋሪዎች መካከል አምስቱ በግብፃዊው ሞሐመድ አታ የሚመሩ ጠላፊዎች ነበሩ።
አውሮፕላኑን የመጥለፍ ሐሳብ የተጠነሰሰው አፍጋኒስታን ውስጥ በአል ቃይዳ ነው።
አስላማዊ ጽንፈኞችን የአውሮፕላን በረራ አሰልጥኖ አሜሪካ ላይ ጥቃት የመሰንዘር እቅድ ጠንሳሽ ፓኪስታናዊው ካሊድ ሼህ ሞሐመድ ነው።
እቅዱን የሳዑዲው ሚልየነር እና የዚያን ጊዜው የአል ቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን አጽድቆታል።

08:14
ከቦስተን አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ቁጥሩ ዩኤ175 የሆነ አውሮፕላን ወደ ሎስ አንጀለስ በረራ ጀመረ። 9 ሠራተኞች እና 56 ተሳፋሪዎች ይዞ ነበር።
በዚህ ደቂቃ በኤኤ11 በረራ ላይ የነበሩት ጠላፊዎች የበረራ ቁጥጥር ክፍል ገቡ።
ሁለት የመስተንግዶ ሠራተኞች በስለት ከተወጉ በኋላ አታ የተባለው ጠላፊ ወደ ቢዝነስ በረራ ክፍል አቀና። አምስተኛው ጠላፊ አንድ ተሳፋሪ በስለት ወግቷል።
ከጠላፊዎቹ መካከል አውሮፕላን ማብረር የሚችለው ሞሐመድ አታ ነው።
በስለት የተወጋው ተሳፋሪ ዳንኤል ሌዊን ይባላል። ከአታ ኋላ ነበር የተቀመጠው። ዳንኤል በእስራኤል መከላከያ ውስጥ ለአራት ዓመታት ሠርቷል። የአውሮፕላን ጠለፋውን ለማስቆም ሲሞክር እንደተገደለም ይታመናል።
ተሳፋሪዎች እና የበረራ አስተናጋጆች በአውሮፕላኑ የኋላ ክፍል እንዲሰበሰቡ ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጣቸው።
ቤቲ ኦንግ የተባለች የበረራ አስተናጋጅ ወደ አሜሪካ የበረራ ተቆጣጣሪ ክፍል ደውላ ኤኤ11 እንደተጠለፈ አስታወቀች።

08:20
የበረራ ቁጥሩ ኤኤ77 የሆነ አውሮፕላን ከዋሽንግተን ደለስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሎስ አንጀለስ በረራ ጀመረ። 6 ሠራተኞች፣ አምስት ጠላፊዎችን ጨምሮ 58 ተሳፋሪዎች ነበሩ።
አውሮፕላኖቹ ከአንድ የአሜሪካ ጫፍ ወደ ሌላው የሚጓዙ ስለሆኑ ነው በጠላፊዎቹ የተመረጡት። እነዚህ አውሮፕላኖች 43,000 ሊትር ነዳጅ ተሞልተዋል። ስለዚህም ከፍተኛ ፍንዳታ ማስከተል ይችላሉ።

08:24
ሞሐመድ አታ ለአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ብሎ አንድ ቁልፍ ተጫነ። ያ ቁልፍ ግን ድምጹን ያስተላለፈው ለተሳፋሪዎች ሳይሆን ቦስተን ለሚገኙ የአውሮፕላን ተቆጣጣሪዎች ነው።
አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ አውሮፕላኖች እንደተጠለፉ ተናገረ።
ጠላፊዎቹ የአውሮፕላኑን የግንኙነት መቆጣጠሪያ [ትራንስፖንደር] አጥፍተውት ስለነበር የትኛው አውሮፕላን እንደተጠለፈ፣ ወደየት እየሄደ እንደሆነ፣ በምን ያህል ፍጥነት እየበረረ እንደሚገኝ እና በምን ያህል ከፍታ ላይ እየበረረ እንደሆነ ተቆጣጣሪዎቹ ማወቅ አልቻሉም።
ዜናው የፌደራል አቪየሽ ተቆጣጣሪዎች ጆሮ ደረሰ። አውሮፕላኖች እየተጠለፉ እንደሆነ ለመገንዘብ 30 ደቂቃ ወስዷል። አውሮፕላኖች ማስጠንቀቂያ ስላልተሰጣቸው በመላው አገሪቱ በረራ ቀጠለ።
በዚህ 30 ደቂቃ ውስጥ አራተኛው እና የመጨረሻው አውሮፕላን ተጠለፈ።
08:42
የተባበሩት አየር መንገድ አውሮፕላን የሆነ በረራ ዩኤ93 ከኒው ጀርሲ ኒዋክ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ በረራ ጀመረ። ሰባት ሠራተኞች፣ አራት ጠላፊዎችን ጨምሮ 37 ተሳፋሪዎች ይዞ ነበር።
አውሮፕላኑ 8፡00 ላይ ይነሳል ተብሎ ቢጠበቅም በትራሪክ መጨናነቅ 8፡42 ተነሳ።
ዩኤ93 ሲነሳ ሁለተኛው አውሮፕላን ዩኤ175 በረራ ላይ ሳለ ተጠለፈ።

08:44
ኤኤ11 ከተጠለፈ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ወደ ኒው ዮርክ መጓዝ ጀመረ።
ወደ ጆን ኤፍ ኬኔዲ (ጄኤፍኬ) አየር ማረፊያ እያቀና ነው ተብሎ ስለታሰበ ሌሎች አውሮፕላኖች መንገድ እንዲለቁ የበረራ ተቆጣጣሪዎች መልዕክት አስተላለፉ።
የበረራ አስተናግጇ ማድሊን ስዌኒ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለአሜሪካ አየር መንገዶች ተቆጣጣሪ ኃላፊ ማይክል ውድዋርድ እያሳወቀች ነበር።
ኤኤ11 ወደ ጄኤፍኬ አውሮፕላን ማረፊያ እየበረረ እንዳልሆነ ተናገረች።
“በጣም ዝቅ ብለን እየበረርን ነው። በጣም በጣም ዝቅ ብለን። ፈጣሪዬ ሆይ እጅግ በጣም ዝቅ ብለን ነው እየበረርን ያለነው።”
ከደቂቃዎች በኋላ ግንኙነቱ ተቋረጠ።

08:46
ኤኤ11 ከዓለም የንግድ ማዕከል (ወርልድ ትሬድ ሴንተር) መንታ ሕንፃዎች አንዱ ከሆነው ባለ 110 ፎቅ ሠሜናዊ ሕንጻ ጋር ተላተመ።
በደቡባዊው ሕንጻ 99ኛ ፎቅ ላይ ትሠራ የነበረችው ኮንስታንስ ላበቲ “ባለሁበት ቆሜ ቀረሁ። መንቀሳቀስ አልቻልኩም” ስትል ታስታውሳለች።
ከጥቃቱ ተርፈው በ9/11 መታሰቢያ ሙዝየም ከሚታወሱ አንዷ ናት።
“አውሮፕላኑ እየቀረበ ሲመጣ እያየሁ ነበር” ትላለች።
አውሮፕላኑ ከ93ኛው ፎቅ ጋር ሲላተም በአንድ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው የሞቱት።
ከ92 ፎቅ በላይ ያለውን የሕንፃው ክፍል መድረስ ስላልተቻለ ብዙዎች መውጣት አልቻሉም።
ከአውሮፕላኑ የፈሰሰው ነዳጅ ቢያንስ አንድ አሳንሰር እና ከሕንፃው በታች ያሉ አራት ፎቆችን ከጥቅም ውጪ አድርጓል።
ሙቀቱ 1,000 ሴንቲ ግሬድ ደርሶ፤ ሠሜናዊውን ሕንጻ ብቻ ሳይሆን ደቡባዊው ሕንጻም በጥቁር ጭስ ታፈነ።
ማንም ሰው ከሕንጻው እንዳይወጣ ቢባልም ኮንስታንስን ጨምሮ ብዙዎች በደረጃ እየሮጡ ከሕንጻው ወጥተው አመለጡ።

08:47
የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ከመንታዎቹ ሕንፃዎች አንዱ በአውሮፕላን እንደተመታ ተነገራቸው።
ገና ዝርዝር መረጃ ስላልወጣ የታቀደውን ዕለታዊ ተግባር መፈጸም ቀጠሉ። ለዚያ ዕለት የያዙት እቅድ ‘ኤማ ኢ ብሩከር’ በተባለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለታዳጊዎች መጽሐፍ ማንበብ ነበር።
የመጀመሪያው አውሮፕላን መጠለፉን የአቪየሽን ባለሥልጣን ቢያውቅም ለ20 ደቂቃዎች ያህል ዋይት ሐውስን ጨምሮ ሌላ ዋሽንግተን ውስጥ የሚገኝ ተቋም ገና መረጃው አልደረሰውም።
ምክትል ፕሬዘዳንት ዲክ ቼኒ ዜናውን በቴሌቭዥን ሲያዩ እንደማንኛውም ሰው ተገርመዋል።
በዚህ ደቂቃ ውስጥ ሦስተኛው አውሮፕላን ኤኤ77 ተጠለፈ።

08:56
የመጀመሪያው አውሮፕላን ከሕንጻው ጋር ከተጋጨ ከ10 ደቂቃ በኋላ የደቡባዊው ሕንጻ የመጨረሻው ፎቆች በጭስ እና እሳት ተሸፈነ።
ሰዎች ከ300 ሜትር ላይ ከሕንጻዎቹ ላይ ተምዘግዝገው ሲወድቁም ይታይ ነበር።
09:01
ሁለተኛው አውሮፕላን ዩኤ175 በኒው ዮርክ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ሳይታይ ይበር ነበር።
የአቪየሽን ባለሥልጣን ስለ አውሮፕላኑ መረጃ የደረሰው በጣም ከዘገየ በኋላ ነው።

09:03
ዩኤ175 በደቡባዊው ሕንጻ 77ኛ እና 85ኛ ክፍል አጋማሽ ላይ ተላተመ።
የሠሜናዊው ሕንጻ በከፍተኛ ፍጥነት በሚበር አውሮፕላን ከተመታ ከ17 ደቂቃ በኋላ ነው ጥቃቱ የደረሰበት።
በኒው ዮርክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማሩ።
ሁለተኛው ሕንፃ ሲመታ ኮንስታንስ ከሕንፃው እየወረደች 72ኛ ፎቅ ላይ ደርሳ ነበር።
“72ኛው ፎቅ ላይ ሳለን ከፍተኛ ድምጽ ሰማን። ፎቁም ተናወጠ። ሰዎች ከደረጃው መውደቅ ጀመሩ። የፎቁን መተላለፊያ በጣም አጥብቄ ስለያዝኩት ሳልወድቅ ቀረሁ።”
ከፎቁ እየወረደች ሳለ እሷ ያለችበት ሕንፃ የተናወጠው ሠሜናዊው ሕንጻ ወድቆበት ነበር የመሰላት። ሁለተኛ አውሮፕላን እሷ ካለችበት ሕንፃ ጋር መላተሙን ያወቀችው ቆይታ ነው።
ዩኤ175 ከመጀመሪያው አውሮፕላን በተለየ ወደታች ዝቅ ብሎ ከሕንፃው ጋር በመላተሙ የሕንፃው የላይኛው ክፍሎች ተርፈዋል።
ከ91ኛው ፎቅ በታች ያሉ ክፍሎች ደረጃቸው ባይጎዳም እሳቱ እና ጭሱ ተደራርቦ ሰዎች በደረጃው ሮጠው ለማምለጥ ተቸገሩ።
የአሜሪካ የአደጋ ጊዜ ነጻ የስልክ መስመር 911 ከመቼውም በላይ ተጨናነቀ። ሰዎች ባሉበት ሆነው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን እንዲጠብቁ 911 ላይ እየተነገራቸው ነበር።
ከደቡባዊው ሕንጻ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች መውጣት ችለዋል።

09:05
ፕሬዝዳንት ቡሽ አሁንም ለታዳጊዎች መጽሐፍ እያነበቡ ነበር። የፕሬዘዳንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንድሩ ካርድ ወደ ቡሽ ጠጋ ብሎ በጆሯቸው ስለ ጥቃቱ ነገራቸው።
“ቀውስ ሲፈጠር መሸበር አያስፈልግም። ስለዚህ ከተማሪዎቹ ክፍል ረጋ ብዬ ወጣሁ። ልጆቹን ማስደንገጥ አልፈለግኩም” ሲሉ ያስታውሳሉ።
09:24
ከሁለተኛው የአውሮፕላን ጥቃት በኋላ በአሜሪካ በረራ ታገደ።
የ40 ዓመታት ልምድ ያለው የዩናይትድ ኤርላየንስ ተቆጣጣሪ ኤድ ባሊገር በሥሩ ላሉ በረራዎች በአጠቃላይ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
ማስጠንቀቂያው ሲሰጥ ከሰሙት አውሮፕላኖች አንዱ የሆነው ዩኤ93 የተጠለፈው አራተኛው አውሮፕላን ነበር።
ኤድ “ሁለት አውሮፕላኖች ከዓለም የንግድ ማዕከል ጋር ተላትመዋል። አውሮፕላናችሁ ውስጥ ሰርጎ ገቦች ካሉ አካባቢያችሁን ቃኙ” አለ።
አውሮፕላን አብራሪው ጄሰን ዳህል “ኤድ ምን እያልክ ነው?” ብሎ ለማጣራት ቢሞክርም መልዕክቱ አልደረሰውም።

09:28
የዩኤ93 አብራሪና ረዳቱ የአደጋ ጊዜ ጥሪ ሲያሰሙ ክሌቭላንድ፣ ኦሀዮ ያሉ ተቆጣጣሪዎች ቢሰሙም ምንም ሊረዷቸው አልቻሉም።
ጠላፊዎቹ አውሮፕላኑን ተቆጣጠሩ።
ዩኤ93 የተጠለፈው በረራው ከተጀመረ ከ46 ደቂቃዎች በኋላ ነው።
ጠለፋው የተመራው በሊባኖሳዊው ዚያድ ጃራህ ነው። ተሳፋሪዎቹ ወደ አውሮፕላኑ ጀርባ እንዲሄዱ አዘዘ። ቦንብ ይዘናል ሲል ያስፈራራም ጀመር። በእርግጥ ጠላፊዎቹ ቦንብ አልነበራቸውም።
ተሳፋሪዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው እና በአውሮፕላኑም ስልክ ለቤተሰቦቻቸው መደወል ጀመሩ። ቢያንስ 37 ጥሪዎች ከአውሮፕላኑ ተደርገዋል።
ተሳፋሪዎቹ ስልክ መደወላቸው ጠለፊዎቹን አላስጨነቃቸውም።
ተሳፋሪዎቹ ለቤተሰቦቻቸው ሲደውሉ መንታዎቹ ሕንጻዎች ላይ የደረሰው ጥቃት ተነገራቸው።
09:34
ዋሽንግተን የሚገኘው የፍትሕ ክፍል ሦስተኛው አውሮፕላን መጠለፉን ሰማ።
ጄነራል ቴዎዶር ኦልሰን የተባሉት ኃላፊ ዜናውን የሰሙት ኤኤ77 ላይ ከነበረችው ባለቤታቸው ብሬንዳ ነበር።
ባለቤታቸው ከአውሮፕላኑ ስልክ ደውላ “አብራሪውን ምን ልበለው?” እያለቻቸው ሳለ ስልኩ ተቋረጠ።
የአቪየሽን ባለሥልጣን ኤኤ77 የት እንዳለ ማወቅ እንዳልቻለ ለአሜሪካ የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል አስታወቀ።
ዋሽንግተን ካለው ሮናልድ ሬጋን አውሮፕላን ማረፊያ ተደውሎ አንድ አውሮፕላን ወደ ዋይት ሐውስ እየገሰገሰ መሆኑ ተነገረ።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ጥብቅ ቦታ ተዛወሩ።
ድንገት ግን አውሮፕላኑ በ330 ዲግሪ ታጠፈ። ዋይት ሐውስን ትቶ ወደ ፔንታገን ያቀና ጀመር።
ፔንታገን ከዋይት ሐውስ 8 ኪሎ ሜትር ይርቃል። አውሮፕላኑ በሰዓት 850 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ወደ ፔንታገን በረረ።
09:37
ኤኤ77 የፔንታገንን ምዕራባዊ ክፍል መታ። የፈጠረው ንቅናቄ ከመሬት 60 ሜትር ከፍ ብሎ እርግብግቢቱ ይሰማ ነበር።
አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 64 ሰዎች በአጠቃላይ እና በአገሪቱ መከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ ውስጥ የነበሩ 125 ሰዎች ሞቱ። በርካቶች ደግሞ ክፉኛ ቆሰሉ።
በመንታ ሕንጻዎች መመታት የተደናገጠው ማኅበረሰብ ስለ ፔንታገን ብዙ አላወራም።
ቡሽ ግን “የመጀመሪያው የአውሮፕላን ግጭት አደጋ ነበር ብንል ሁለተኛው ደግሞ ግልጽ ጥቃት ነው። ሦስተኛው ግን የጦርነት አዋጅ ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ዘጋቢ ተናግረዋል።

09:42
የአቪየሽን ባለሥልጣን ሁሉም አውሮፕላኖች በአቅራቢያቸው ካለ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲቆሙ አዘዘ።
ትዕዛዙ ሲተላለፍ አንድ ተጨማሪ የተጠለፈ አውሮፕላን አየር ላይ ነበር። ዩኤ93። የግንኙነት መሳሪያው ስለጠፋ የት እንዳለ ማወቅ አልተቻለም።
09:57
የዩኤ93 ተሳፋሪዎች እና የበረራ አስተናጋጆች ጠላፊዎቹን ለማስቆም አንዳች እርምጃ ካልወሰዱ ሊያልቁ እንደሆነ አመኑ።
የቀድሞዋ የበረራ አስተናግጅ አሊስ ሆግላንድ አውሮፕላኑ ውስጥ ለነበረው ልጇ ሁለት የድምጽ መልዕክት ላከች።
አንደኛው መልዕክት፡ “ልጄ ማርክ አውሮፕላኑ በአሸባሪዎች ተጠልፏል። አውሮፕላኑን ከአንዳች ሕንጻ ጋር አላትመው ጥቃት ማድረስ አቅደዋል። አሸባሪዎቹን ለማስቆም የቻልከውን ሁሉ አድርግ።”
ሁለተኛው መልዕክት፡ “አንድ አውሮፕላን ወደ ሳን ፍራንሲስኮ እየሄደ ነው ተብሏል። ያ አውሮፕላን አንተ ያለህበት መሰለኝ። ጥቂት ሰዎችን ሰብስበህ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ሞክሩ። መልካም እድል። እወድሀለው። ቻው።”
አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች ጠላፊዎቹን ለማስቆም ተስማሙ።

09:58
በዚህ ሰዓት ደቡባዊው ሕንጻ በ11 ሰከንድ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተደርምሶ ወደቀ።
ሕንጻው ውስጥ ያሉ ሰዎች በአጠቃላይ፣ መንገድ ላይ የነበሩ ሰዎችም ጭምር ሞቱ።
ኮንስታንስ ከመንታዎቹ ሕንጻዎች ከተረፉ አንዷ ናት። ከሕንጻው ሮጣ እንድትወጣ ያበረታታት አለቃዋ ፋዚዩ ግን በጥቃቱ መሞቱን ትናገራለች።
10:03
የዩኤ93 ተሳፋሪዎች በአውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ ክፍል ገብተው ጠላፊዎቹን ለማስቆም ለስድስት ደቂቃዎች ታግለዋል።
የመቆጣጠሪያውን ክፍል በር ለመክፈት ሲሞክሩ እቃ ሲሰባበር እና ሲገለባበጥ ይሰማ ነበር።
ከጠላፊዎቹ አንዱ ጃራህ “እንጨርስ?” ሲል ጠየቀ። ሌለው ጠላፊ ግን “ገና ነው። ሁሉም ሲሰበሰቡ እንጨርሳለን” ብሎ መለሰ።
ኢላማቸው ከሆነው ዋሽንግተን ዲሲ በ20 ደቂቃ ርቀት ላይ ነበሩ።
ጃራህ በድጋሚ ጠየቀ “አውሮፕላኑን እንከስክሰው?”
ሌላኛው ጠላፊ መለሰ “አዎ”
ዩኤ93 ውስጥ ድምጽ ተሰማ “አላህ ታላቅ ነው። አላህ ታላቅ ነው።”
አውሮፕላኑ ፔንሲልቬንያ ሜዳ ላይ ተከሰከሰ። በሰዓት 930 ኪሎ ሜትር ይጓዝ ከነበረው አውሮፕላን ማንም በሕይወት አልተረፈም።
የአውሮፕላኑ ኢላማ ዋይት ሐውስ ወይም ካፒቶል ሂል ነው ተብሎ ስለታመነ የአሜሪካ መከላከያ አውሮፕላኑን መትቶ ለመጣል ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር።

10:28
ኤኤ11 ከሠሜናዊው ሕንጻ ጋር ከተጋጨ 100 ደቂቃዎች አለፉ። በዘጠኝ ሰከንድ ልዩነት ደግሞ ሌላኛው ሕንፃ ተመታ።
የኒው ዮርክ እሳድ አደጋ ሠራተኛው ቢል ስፔድ ከሠሜናዊው ሕንጻ በጥቂት ደቂቃዎች ርቀት ላይ ነበር።
ፍንዳታው 12 ሜትር ገፍቶ ነው የጣለው። ያለበትን ለማወቅ አንድ ሰዓት ያህል አስፈልጎታል። ከ12 የሥራ ባልደረቦቹ መካከል በሕይወት የተረፈው እሱ ብቻ ነበር።
በዩኤ93 ተሳፍሮ የነበረው አጎቱ ሞቷል።
ከ19ኙ ጠላፊዎች ውጪ 2,977 በጥቃቱ ሞተዋል። አሜሪካ ላይ የደረሰው ከባዱ የሽብር ጥቃታም ነው።
9/11 በአሜሪካ ታሪክ በርካታ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሞቱበት ነው። ኒው ዮርክ ውስጥ ብቻ 343 የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሞተዋል።
በተጨማሪም 400,000 ሰዎች ለመርዛማ ጭስ ተጋልጠዋል። ከጥቃቱ ከወራት በኋላ ብዙዎች ሞተዋል። በጠና የታመሙ እና የሥነ ልቦና ቀውስ የገጠማቸውም አሉ።
አሜሪካ ኦሳማ ቢል ላደንን ለመያዝ የአል ቃይዳ ምሽግ ናት የተባለችውን አፍጋኒስታን በ2001 ወረረች።
ቡሽ “ከሽብር ጋር ጦርነት” ያሉት ዘመቻ 2003 ላይ ኢራቅን ወደ መውረር ተሻገረ።
9/11 ከደረሰ ሁለት አሰርታት ተቆጥረዋል። አሜሪካም ከአፍጋኒስታን ወጥታለች።
የአሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣት ወደ ሌላ ነውጥ እና ግራ መጋባት አምርቷል። ታሊባን ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ሥልጣን ተመልሷል።
አሁን ካለውም የባሰ ቀውስ ሊነሳ እንደሚችልም ተሰግቷል።
