ሰሜን ኮሪያ አብዛኛውን የጃፓን ክፍል ሊመታ የሚችል አዲስ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ሙከራ ማካሄዷን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘገበ።
ቅዳሜና እሁድ በተካሄዱት ሙከራዎች ሚሳይሎቹ እስከ 1,500 ኪ.ሜ ርቀው ስለመጓዛቸው ኮሪያን ሴትንራል የዜና ማዕከል ዘግቧል።
ሙከራው አገሪቱ ካለችበት የምግብ እጥረት ብሎም የኢኮኖሚ ቀውሶች ችግር ባሻገር አሁንም የጦር መሳሪያዎችን የማምረት አቅም እንዳላት ያመላከተ ነው ተብሏል።
ይህ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ሙከራ “በተለይም የአገራችንን ደህንነት ለማስጠበቅ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ስትራቴጂካዊ የሆነ ጥቃትን የማስቆም አቅም የሚያስገኝ ብሎም የጠላት ኃይሎችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማስቆም የሚያስችል ይሆናል” ሲል ኬሲኔንኤ ዘግቧል።
- ሰንበሬ ክብረ ወሰን ስታሻሽል ማራቶን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ ውጤቱ ተሰረዘበት
- የ13 ወራት ባለፀጋዋ ኢትዮጵያ
- በትግራይ ክልል ለነዋሪዎች የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደናቀፍ እና እንዲሻሻል ተጠየቀ
የጃፓን ካቢኔ ዋና ፀሐፊ ካትሱቡ ካቶ በበኩላቸው ጉዳዩ መንግሥታቸውን ያሳሰበ መሆኑን እና መፍትሄውን በተመለከተም ከአሜሪካ እና ከደቡብ ኮሪያ ጋር እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ የጦር ኃይል ሙከራው ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ መርሃ ግብሯን የማሳደግ ያላትን እቅድ ብሎም ለጎረቤቶቿም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የደቀነችውን ስጋት ያሳያል ሲል ድርጊቱን አውግዟል።
አክሎም አሜሪካ ወዳጅ አገሮቿ የሆኑትን ደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን ለመከላከል የያዘችው ቁርጠኛ አቋም አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይል ዮናፕ ለተሰኘው የዜና ወኪል እንደገለጸው ከአሜሪካ የስለላ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራን የተመለከተ ጥልቅ ትንታኔ እያካሄደ ይገኛል።
በተያዘው ሳምንት ውስጥም ከአሜሪካ፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ከጃፓን የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ለውጥ ሂደት ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ከመሞከር አግዷታል።
ምክር ቤቱ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ከፍተኛ አረር ስለሚይዙ፣ ረጅም ርቀት ስለሚጓዙ እና ፈጣን ስለሆነ እንደ ስጋት ይመለከታቸዋል።