የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በሰሃራ በረሃ አካባቢ የኢስላሚክ ስቴት አዛዥ የነበረው ግለሰብ በፈረንሳይ ወታደሮች መገደሉን አስታወቁ።
አድናን አቡ ዋሊድ አል-ሳሃራዊ እአአ 2015 ላይ የግሬተር ሳሃራ ኢስላሚክ ስቴት የተባለውን ጽንፈኛ ቡድን አቋቁሞ ነበር።
ይህ ቡድን በሰሜን አፍሪካ ቀጠና ለሚደርሱ የሽብር ጥቃቶች ተጠያቂ ሲደረግ ቆይቷል። እአአ 2020 ላይ የፈረንሳይ ዜጎች የሆኑ የእርዳታ ሠራተኞችን ላይ በፈጸመው ጥቃት ስለመግደሉም ተዘግቦ ነበር።
ማክሮን የቡድኑን መሪ ግድያ “በሳህል ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር የምናደርገው ትግል ጉልህ ስኬት ነው” ብለዋል።
- የአዲስ አበባ የ60ዎቹ የኪነ ህንፃ መለያዎች ‘እድሳት’ እና ያስነሳው ጥያቄ
- በትግራይ በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የጦር ወንጀል ተፈፅሟል – የመብት ተሟጋች ቡድን
- የጋናው የቁንጅና ውድድር እና ኢትዮጵያን የወከለችው ተወዳዳሪ
- የፀጥታው ምክር ቤት የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ መግለጫና የኢትዮጵያ አቋም
ሳህል 1.16 ሚሊዮን ስኩዌር ማይል ስፋት ያለው ከደቡብ ሰሃራ በረሃ እስከ ምዕራብ ሴኔጋ፤ ከምዕራብ ሴኔጋ እስከ ምሥራቅ ሶማሊያ የተዘረጋ ሰፊ አካባቢ ነው።
ፕሬዝደንት ማክሮን የአድናን አቡ ዋሊድ አል-ሳህራዊ ግድያ ኦፕሬሽንን በተመለከተ ማብራሪያ አልሰጡም።
የፈረንሳይ መከላከያ ሚንስትር ፍሎረንስ ፓርለይ በትዊተር ገጻቸው፤ ሳህራዊ የተገደለው ባርካህን ኃይል በተባለ የፈረንሳይ ጦር ኦፕሬሽን ነው ብለዋል።
ይህ የፈረንሳይ ኃይል በሳህል በተለየ ደግሞ በማሊ፣ ኒጀር፣ ቻድ እና ቡርኪና ፋሶ እስላማዊ ጽንፈኞችን ይዋጋል።
መከላከያ ሚንስትሯ በተመሳሳይ የቡድኑ መሪ መገደል፤ “ለሽብርተኛ ቡድኑ ትልቅ ውደቀት ነው” ካሉ በኋላ “ትግሉ ይቀጥላል” ብለዋል።
ሳህራዊ በሞሮኮ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባት ምዕራብ ሰሃራ ውስጥ እአአ 1973 የተወለደ ሲሆን ከሞሮኮ ነጻነትን ለመቀናጀት የፖሊሳሪዮ ግንባር አባል ሆኖ ሲዋጋ ነበር።
ቆይቶም በማግሬብ አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን የአል-ቃኢዳ ቡድንን ተቀላቅሎ ሲመራ ነበር። ይህ የማሊ እስላማዊ ቡድን እአአ 2012 ላይ የስፔን ዜግነት ያላቸውን እርዳታ ሠራተኞች አልጄሪያ ውስጥ አግቶ ነበር። በተመሳሳይ ዓመት ማሊ ውስጥ የአልጄሪያ ዲፕሎማቶችን አፍኖ ወስዶም ነበር።
ባለፈው ነሐሴ ወር የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ስድስት የፈረንሳይ ዜጎች የሆኑ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እና ናይጄሪያውን አሸከርካሪዎቻቸው እንዲገደሉ ሳህራዊ ትዕዛዝ ሰጥቷል ብለው ነበር።
ይህ ቡድን እአአ 2019 ላይም በማሊ እና ኒጀር በወታደር ካምፖች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ቆይቷል።
እአአ በ2017 ላይ ደግሞ በማሊ በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች የተገደሉበትን ጥቃት ያቀነባበረው ይህ በሳህራዊ የሚመራ ቡድን ነበር ተብሏል።
በሳህል ቀጠና ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የዕጽ አዘዋዋሪዎች እና ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች በስፋት ይንቀሳቀሳሉ።
ጂሃዳዊ ጥቃቶችም ወደ ጎረቤት ናይጄሪያ ተዛምተው በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።