10 መስከረም 2021

ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ 13 ተርባይኖች መካከል ሁለቱ ተርባይኖች በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ለቢቢሲ ገለጹ።
“ኃይል ማመንጨት የምንጀምረው ከሁለቱ ተርባይኖች ነው። ይሄ ኧርሊ ጀነሬሽን [የመጀመሪያ ደረጃ የኃይል ማመንጨት] ነው። ሁለቱ ተርባይኖች የሚያመጩት ኃይል እስከ 750 ሜጋዋት ይደርሳል” ሲሉ ሚንስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በ2014 ዓ. ም የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ከሁለቱ ተርባይኖች የሚመነጨው ኃይል ጥቅም ላይ መዋል እንደሚጀምር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ አክለዋል።
እያንዳንዱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ከ375 እስከ 400 ሜጋዋት የሚደርስ ኃይል ያመነጫሉ።
የሕዳሴ ግድቡ 6450 ሜጋዋት ኃይል ማምረት ይችላል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍጆታ 10.7 ሚሊዮን ኪሎዋት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከሕዳሴ ግድቡ የሚገኘውን ኃይል ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ የሚተርፈውን ማለትም 2000 ሜጋዋት ያህሉን ለጎረቤት አገራት በመሸጥ በዓመት እስከ 580 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚቻል ይገመታል።
- “ወደድንም ጠላንም ከአንድ ወንዝ ስለምንጠጣ መተባበርን መማር አለብን” ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር)
- አሜሪካ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት መሪነት መቀጠል አለበት አለች
- ስለ ዓባይ ወንዝ እና የሕዳሴ ግድቡ ጥቂት እውነታዎች
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ የሚገኘው የሕዳሴ ግድቡን ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ 80 ቢሊየን ብር (ከ4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ) እንደሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
የዋናው ግድብ ውፍረት የግድቡ ግርጌ ላይ 130 ሜትር ሲሆን፤ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል ደግሞ 11 ሜትር ነው።
ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፤ ግድቡ የሚሸፍነው የቦታ ስፋት ደግሞ 1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት የመጀመሪያው ዙር የግድቡ ሙሌት ተከናውኗል። በዚህም 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ ዕቅዱ ተሳክቷል።
በያዝነው ዓመትም የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ተካሂዷል። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በ2013 ዓ. ም. በሐምሌ ወር 6.9 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ እንዲሁም በነሐሴ ወር ተመሳሳይ መጠን ያለው ውሃ እንደሚሞላ ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባት ከ80% በላይ እንደተጠናቀቀ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ላለፉት አስር ዓመታት ገደማ በሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ዙርያ ከኢትዮጵያ ጋር ሲወዛገቡ የነበሩት ግብፅ እና ሱዳን ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደወሰዱት አይዘነጋም።
ምክር ቤቱ ግን የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት የበላይ አሸማጋይነት መፍትሔ እንዲሰጠው ምክረ ሐሳቡን ሰጥቷል።
በወቅቱ ለምክር ቤቱ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ “ወደድንም ጠላንም ከአንድ ወንዝ ስለምንጠጣ መተባበርን መማር አለብን” በማለት ሦስቱ አገራት በዓባይ ዙርያ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም።
